የከተማ ግብርናን ውጤትማነት ይበልጥ ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ ግብርናን ውጤትማነት ይበልጥ ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦ በከተማ ግብርና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል በዘርፉ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና ልምዶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ጥናት ይፋ አድርጓል።
ኢንስቲትዩቱ ጥናቱን ላለፉት ስድስት ወራት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት እርባታና በንብ ማነብ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዲሪባ ገለቲ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የከተማ ግብርና ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠርና ምርታማነትን በመጨመር ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው።
ይሁንና በመዲናዋ እየተካሄደ ያለው የግብርና ሥራ የመዋቅር ክፍተት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችና በዘርፉ ብቃት ያለው የባለሙያ እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል።
የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ እንዲመታ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መረባረብ አለበት ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ የግብርና ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶክተር ቶለሳ አለሙ በበኩላቸው ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ ያለመሟላት ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ አቅርቦት ችግር በአመራረቱ ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን በጥናቱ መገኘቱን ገልጸው ችግሮቹን ለመፍታት የዘርፉን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት።
የእንስሳት እርባታና የእርሻ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው ቦታዎች ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም አንስተው ተረፈ ምርቱን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያና ባዮጋዝ የሚለማበት ሁኔታዎች ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በግብርና ሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያካሄደ ይገኛል።
ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ ተገልጿል።