በኢትዮጵያ የ10 ዓመት የወተት ልማትና የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ትግበራ ገብቷል

አዳማ ፤ታህሳስ 16/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የ10 ዓመት የወተት ልማትና የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መግባቱ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የወተት ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ውጤታማ አጋርነትና ትብብር ለመፍጠር ያለመ መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በሀገሪቷ የምግብና ስነ ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል የእንስሳትና ወተት ሀብት ልማት ስራ አንዱ መሆኑን ገልጿል።

በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ዝርያን ከማሻሻል ጀምሮ የወተት ልማት ስራ ቀዳሚ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በዳልጋ ከብቶችና በግመል ልማት ላይ የዝርያ ማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመት ብቻ በአገሪቷ 2 ነጥብ 2 ሚሊዬን እንስሳትን ለማዳቀል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የእንስሳት መኖ ልማትና ጤና ላይ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ፍቅሩ፤ የኮርማ አባለዘር ከማምረትና ከማቅረብ አኳያ የተሻለ ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።


 

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩን ይበልጥ ለማሳካት እንዲያስችልም የ10 ዓመት የወተት ልማትና የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም ዓመታዊ የወተት ምርቱን "በዓለም የጤና ድርጅት በአማካይ ዜጎች በነፍስ ወከፍ በዓመት ማግኘት ያለባቸውን 200 ሊትር ተደራሽ ለማድረግ ግብ አስቀምጠን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።

በተጨማሪም የምርት ጥራትና አቅርቦት እንዲሁም የዘርፉን ልማት የማዘመን ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የሌማት ትሩፋትንም ሆነ የወተት ልማት ስትራቴጂን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የወተት ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንስሳቱን በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ ሳይንሳዊ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማዳቀል ስራ እንዲከናወን የዝርያ አቅርቦትና ሙያዊ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የወተት ልማቱን ጤንነትና ደህንነት የማስጠበቅ፣ የአቅርቦት፣ የማጓጓዝና የማቀነባበር ሥራ ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም