በኮንስትራክሽን ዘርፍ በልምድ የተሰማሩ ባለሙያዎች ክህሎትን ለማዳበር የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኮንስትራክሽን ዘርፍ በልምድ የተሰማሩ ባለሙያዎች ክህሎትን ለማዳበር የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዜጎች በልምድ ያገኙትን ክህሎት በማካበት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦቪድ ግሩፕና ከጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ በልምድ የተገኘ የሙያ ብቃት ምዘና የእውቅና መርኃ-ግብር አካሂዷል።
ምዘናውን በጄኔራል ዊንጌት ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የተሰጠ ሲሆን በግንበኝነት፣ በለሳኝነት፣ በቀለም ቀቢነትና በአጠቃላይ በመሰረታዊ የግንበኝነት ሙያ ምዘና ተደርጎላቸዋል።
በዚህም 62 የኦቪድ ኮንስትራክሽን ሠራተኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘናውን የወሰዱ ሲሆን 45 ሠራተኞች ምዘናውን አልፈው የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።
በዚሁ ወቅት የተገኙት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዶክተር ተሾመ ለማ እንዳሉት ዜጎች በልምድ ያገኙትን እውቀት ለማካበት አሰራር እየተዘረጋ ነው።
በዚህም ዜጎች በኢ-መደበኛ ሥርዓት ያገኙትን ብቃት (ዕዉቀት፣ ክህሎትና የሥራ ዝንባሌ) በሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና ሥርዓት መመዘን አንዱ ነው ብለዋል።
ምዘናው ዜጎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ የሙያ ሥልጠና እንዲሁም የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት።
በመሆኑም በቀጣይ በኢ-መደበኛ ኢኮኖሚ ዉስጥ የተሰማራዉን የሰዉ ኃይል ብቃት የሚረጋገጥበትን ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኦቪድ ኮንስትራክሽን የቢዝነስ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ያሬድ ወንዴ፤ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ለማጠናከር ብቁ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለዚህም በኦቪዲ አካዳሚ የሙያ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ተመዝነው ዛሬ እውቅና የተሰጣቸው የድርጅቱ ባለሙያዎችም ለበለጠ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት እንዲተጉ የሚስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የብቃት መረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያገኙ አቶ ሁሰን አሊና አቶ መልካሙ ተስፋ ምዘናው በሥራ ገበያዉ ተወዳዳሪና እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ያስችለናል ብለዋል።