ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከየካቲት 9 ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከየካቲት 9 ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ለ9ኛ ጊዜ የሚካሔደውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

 ሚኒስትሯ  በመግለጫቸውም ፎረሙ "የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል የሚካሔድ መሆኑን ተናግረዋል።

ፎረሙን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመሆን በቅንጅት የሚያዘጋጁት መሆኑን ተናግረዋል።

የዘርፉ ተዋንያንን በማስተባበር  ወደፊት ተራማጅ እንዲሆኑ ማስቻልም የፎረሙ ዋነኛ አላማ መሆኑንም  ገልጸዋል።

የከተሞች የእርስ በእርስ ትውውቅ እንዲሁም የከተሞችን እምቅ አቅም መለየት ከፎረሙ ከሚጠበቁ ውጤቶች መካከል መሆናቸውን እንዲሁ ።

ፎረሙ በከተሞች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲኖር ከማገዙ ባለፈ በዝግጅቱ ላይ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውም ከተሞችም እውቅና እንደሚሰጣቸው አመላክተዋል።

በፎረሙ ላይ በመስኩ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ዝግጅቶችም እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ ብርሀኑ ዘውዴ፤ በበኩላቸው ክልሉ አዲስ የተመሰረተ እንደመሆኑ ፎረሙን ለማዘጋጀት የተሰጠው ዕድል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ፎረሙ ከተሞችን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ የሚጠበቀውን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ለስምንት ጊዜ በተለያዩ ከተሞች በደማቅ ሁኔታ መከበሩ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም