ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የተከሰቱት የደንጊ እና የወባ በሽታዎችን የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር  መልክ የተከሰቱት የደንጊ እና የወባ በሽታዎችን የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ ገለጹ።

ባለፉት ወራት በድሬዳዋ አስተዳደር የወባ እና የደንጊ ትኩሳት በሽታዎች  ተከስተው በብዙ ሺህ የሚገመቱ ነዋሪዎች ለሕመም ተዳርገው ቆይተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  የተከሰቱትን በሽታዎች በተቀናጀ መንገድ የመከላከልና ሕክምና የመስጠት ሥራ በመስራቱ ተጭባጭ ውጤት መጥቷል። 

በአስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታን በቁጥጥር ስር ለማዋል መቻሉን አስታውሰው፣ ዘንድሮ በተለየ መንገድ የተከሰተው የደንጊ ትኩሳትና የወባ በሽታ በሕክምና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ገልጸዋል።

የበሽታዎቹን ስርጭት ለመከላከል በከንቲባ የሚመራ ግብረ ኃይል ከማቋቋም ባለፈ በህዝብ ንቅናቄ የትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን የማፅዳትና ፍሳሾችን የማድረቅ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በበሽታ ለተያዙ ሰዎችም አስፈላጊውን ሕክምና ከመስጠት በተጨማሪ በተመረጡ አካባቢዎችና ቤቶች የኬሚካል ርጭት በማካሄድ የተሻለ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ዶክተር ጽጌረዳ ተናግረዋል።

በተለይ ነዋሪዎች በሙሉ አቅማቸው በጽዳት ሥራዎች መሳተፋቸውና በአስተዳደሩ የሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ቀበሌዎች ከጤና ተቋማት ጋር ተቀናጅተው መስራታቸው  በሽታውን ለመቆጣጠር እያስቻለ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በአሁን ወቅት በበሽታዎቹ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ሲሆን የነበረው የሞት አደጋም የለም።

እንደ ዶክተር ጽጌረዳ ገለጻ በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው።

በተለይ የበሽታ አስተላላፊ ትንኞች የሚፈለፍሉት ዕንቁላል ለስምንት ወራት የሚቆይ በመሆኑ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።


 

የድሬዳዋ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ባህሩዲን አህመድ በበኩላቸው በተከሰተው ወረርሽኝ ጤና ጣቢያውና ባለሙያዎቹ ሌት ተቀን ህይወት ለማዳን እየተረባረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ወራት በጤና ጣቢያው ባዶ ቦታዎች ላይ ጭምር ለሕሙማን ሕክምና ሲሰጥ መቆየቱንም አስታውሰዋል። 

ጤና ጣቢያው ከቀበሌና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የትንኝ መራቢያ ሥፍራዎች እንዲጸዱ በማድረግና ለህብረተሰቡ ተገቢውን ህክምና በመስጠቱ በሽታዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ያሉት ደግሞ ሲስተር ትዝታ ታደሰ ናቸው።


 

በአሁን ወቅት በወባና ደንጊ ትኩሳት በሽታዎች ተይዘው ሕክምና ፍለጋ ወደጤና ጣቢያው የሚመጡ አዲስ በሽተኞች የሉም ብለዋል።

በድሬዳዋ የከዚራ ነዋሪ ወይዘሮ የሺ አስፋው በበኩላቸው ለታመሙ ሰዎች በጤና ጣቢያ ተገቢውን ህክምና እና እንክብካቤ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል። 

ለነዋሪዎች የተሰጠው የመከላከያ ትምህርት ሁሉም የአካባቢውንና የቤቱን ንፅህና እንዲጠብቅ አስችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለትንኝ መራቢያ የሆኑ ቦታዎችን የማፅዳት ስራን ቀጥለናል ብለዋል።

የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ዘንድሮ በተለየ መንገድ የተከሰተውን በሽታ ተከትሎ ከጤና ሚኒስቴርና ከምርምር ማዕከላት ጋር በመሆን ለዘላቂ መፍትሄ ሥራ የጀመረ ሲሆን ከተጎራባች ክልሎች ጋርም በመቀናጀት ስራ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም