ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ የጀመሩትን ሥራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ዓላማና የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለሕዝቡ ለማስገንዘብ የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል። 

በውይይቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። 

በውይይቱም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ አፈጻጸም ላይ የመስክ ምልከታን አስመልክቶ ሪፖርት ቀርቧል። 

በዚህም ቋሚ ኮሚቴው በሲዳማ፣ ሀረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴን መመልከቱ ተገልጿል።


 

በዚሁ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ በአገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በዋና ዋና ጉዳዮቻቸው ላይ መግባባትን በመፍጠር የተሻለች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል። 

ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተደረገ ያለው እገዛም ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ለማስወገድ ከፍተኛ ፍላጎት ያለ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልፀዋል።

መንግሥት  የተሻለ መግባባት የተፈጠረባትና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስቀጠል አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወሳኝ በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እያረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ እንቅስቃሴ ሂደትም መገናኛ ብዙኃን እያከናወኑት የሚገኘውን የተግባቦት  ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። 


 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ በቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ መነሻነት በጥንካሬ የቀረቡ ጉዳዮችን በማስቀጠል በድክመት የተነሱ አስተያየቶችን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል። 

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬትም ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመምህራን፣ ከእድሮች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ከሌሎች አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በሂደቱም የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማና እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን መገናኛ ብዙኃን በተግባቦት ሥራዎቻቸው ማኅበረሰቡን በማሳወቅና በማስገንዘብ እገዛቸውን እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል። 

የውይይቱ ተሳታፊ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎችም የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማ እውን ተማድረግ አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርጉ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትም ብሔራዊ ምክክር ሂደት በመሆኑ ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም