የአቅም ግንባታ ስልጠናው በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት እንድንገነባ አግዞናል- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የአቅም ግንባታ ስልጠናው በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት እንድንገነባ አግዞናል- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች
ጂንካ፤ ታህሳስ 16/ 2016(ኢዜአ)፦ ከአቅም ግንባታ ስልጠናው ካገኙት ዕውቀት በመታገዝ በተቋማት የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማፅዳት ለህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ"ዕዳ ወደ ምንዳ" በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ከተማ ስልጠና የተከታተሉ የማህበራዊ ክላስተር የመንግስት ሰራተኞች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሥልጠናው በዕውቀትና በክህሎት እንድንገነባ አድርጎናል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ፍሬህይወት በቀለ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከአቅም ግንባታ ስልጠናው በርካታ ዕውቀትና ልምድ እንዳገኙበት ገልፀዋል።
በዚሁ በመታገዝ በቀጣይ ለህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የልማት ተግባራት እንዲፋጠኑ የሚጠበቅብኝን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ነው ያሉት።
የአቅም ግንባታ ስልጠናው በዚህ ወቅት መሰጠቱ ሰራተኛው ራሱን በእውቀትና በአመለካከት በመገንባት በአዲስ አስተሳሰብና በላቀ ትጋት ህዝቡን እንዲያገለግል ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
በተቋማት በተለይ ከደረጃ ዕድገት፣ ዝውውርና ከሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ግድፊቶችን ሙሉ ለሙሉ በመቅረፍ ከአድሎና ከብልሹ አሰራር የፀዳ ተቋም ከመገንባት አኳያ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን ብለዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠናው የመንግስት ሰራተኛው በዕውቀት፣ በአመለካከትና በክህሎት አንድ እንዲሆን ያግዛል ያሉት ደግሞ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባለሙያ አቶ በኃይሉ ዘብዲዮስ ናቸው።
በዚህም በተቋማት ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት አመቺ ነው ያሉት አቶ በኃይሉ ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ለህዝቡ ያለምንም ቢሮክራሲ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ባለሙያ አቶ ተፈሪ ነጋ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና የተቋማትን ራዕይና ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
አገራዊ ራዕይና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀው ይህንንም ማሳካት የሚያስችል አቅም አግኝተናል ነው ያሉት።
በቀጣይም ወጣቱን ያሳተፈ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በመቅረፅ በተለያዩ የስራ መስኮች ወጣቱን በማሳተፍ የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደፋሩ እንደገለፁት፤ በየጊዜው የሰራተኛውን አቅም በማጎልበት የህዝቡን አዳጊ የልማትና የዕድገት ፍላጎት ለማሟላት እንዲተጋ ለማስቻል ተከታታይ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።
ክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥንና የፍትሃዊ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በብዝሃ ማዕከላት ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።
በሁሉም ማዕከላት እስከታች ድረስ ባሉ መዋቅሮች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተከታታይ ስልጠናው መሰጠቱን ገልጸዋል።
የተጀመረው የተቋም ግንባታ ውጤታማ እንዲሆን የአመራሩና የፈፃሚ ባለሙያዎች ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በዚህም አመራሩና ሰራተኛው ተቀናጅቶ በመስራት ከህዝቡና ከመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።