ኢትዮጵያ በሦስት ዓመት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን እቅድ ይዛ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሦስት ዓመት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን እቅድ ይዛ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣይ ሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድርና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጠና ሥምምነትን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ባደረገቻቸው የአራት ዙር ድርድሮች የድርጅቱ 164 አባል ሀገራት ላቀረቧቸው 900 ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቷን ገልጸዋል።
ሀገራቱ በዕቃዎችና የአገልግሎት ንግድ፣ የገቢ ንግድ ፈቃድ አሰራር መረጃዎች፣ የመንግሥትና የንግድ ድርጅቶች መረጃና ሌሎች ጥያቄዎች ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
በአምስተኛው ዙር ድርድር ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁንና ለዚህ ተልዕኮ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የጥናት ሰነዱን እየገመገመ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በሦስት ዓመት ውስጥ የድርጅቱ አባል ለመሆን እየሰራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ባለኃብቶች የተለያዩ ኢኮኖሚ መስኮችን ክፍት ለማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጓ ድርድሩ እንዲሳለጥ እድል ፈጥሯልም ነው ያሉት።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ሀገራት ተወዳዳሪነታቸው በመጨመርና ምጣኔ ኃብታቸው እንዲያድግ እድል እንደሚፈጥርላቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በድርድር አባል ለመሆን በታዛቢነት መሳተፍ የጀመረችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2003 ነበር።
ይሁንና በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሌሎች ምክንያቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ድርድሩ ተቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ነው።