የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠት ሊንቀሳቀሱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠት ሊንቀሳቀሱ ይገባል
ሆሳዕና፤ታህሣሥ 16/2016 (ኢዜአ )፡- በክልሉ የሚገኙ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመከባበር፣ በመተሳሰብና ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው አስገነዘቡ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብን የልማት ፍላጎቶችን ለመሙላት የሚያስችል ሥራን በተቀናጀ መንገድ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ለዚህም የሀገረ መንግስት ግንባታው በሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ተደግፎ እውን እንዲሆን የሁሉንም ዜጋ ርብርብ የሚሻ መሆኑንም ተናግረዋል።
"ስለሆነም ፓርቲዎች ተቀራርቦ በመምከር በጋራ መስራት በክልሉ የታቀደው ግብ እንዲሳካና ፈጣን ለውጥ እንዲመዘገብ አጋዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመከባበር፣ በመተሳሰብና ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የበኩላቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
አንድነት፣ እኩልነትና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቢቆዩም የሚጠበቅባቸውን ያህል ውጤት በማስመዝገብ ረገድ ከፍተኛ ተግዳሮት ሲፈጠርባቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።
የለውጡ መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተቀራርበው እንዲሰሩ በፈጠረው ምቹ አጋጣሚ በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግባቢያ ሰነድ በማዘጋጀት ለሀገር እድገት በጋራ መንቀሳቀስ ስለመጀመራቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላም፣ ለልማትና እድገት መረጋገጥ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
በመርሐ ግብሩ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና በክልሉ የሚገኙ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎቲ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።