የጋምቤላና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የሰላምና የልማት የጋራ ፎረም የምስረታ መድረክ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የሰላምና የልማት የጋራ ፎረም የምስረታ መድረክ እየተካሄደ ነው
ቦንጋ ፤ ታህሳስ 16/2016(ኢዜአ) ፡-የጋምቤላና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የሰላምና የልማት የጋራ ፎረም የምስረታ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑሞድ ኡጁሉና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ተገኝተዋል።
እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ በመክፈቻ ንግግራቸው "ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ የመንግስትና የማህበረሰብ የጋራ ትብብር ውጤቶቸ ናቸው" ብለዋል።
ሰላምን በማፅናት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን በማሳደግ የልማት አቅሞቻችንን ማሳደግ ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማፋጠን በምናደርገው ርብርብ ውስጥ ሁለቱ ክልሎች ተቀናጅተው ይሰራሉ ነው ያሉት።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦችና የጋምቤላ ክልል መንግስታት ለዘመናት ያቆዩትን የህዝቦች የእርስ በርስ ትብብር ይበልጥ እንዲጎለብት በማድረግ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ማሳደግ ትኩረታችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች ተመሳሳይ የአየር ጠባይ፣ መልክአ ምድርና በርካታ እሴቶችን የሚጋሩ ናቸው ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ።
ይህንን ጠንካራ ትስስር ይበልጥ በማጎልበት በሁለቱ ክልል አጎራባች የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮች ውስጥ የሚከሰቱ የወሰን ጉዳዮችን በተሳካ ሁኔታ ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ህገወጥ የማዕድንና የንግድ እንቅስቃሴዎችን በጋራ መከላከል ህብረተሰቡን ለግጭት የሚገፋፉ ድርጊቶችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል ላይ በትኩረት ይሰራልብለዋል።
ይህ የሚመሰረተው የጋራ ፎረም የሁለቱን ክልሎች ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ስላምንና ልማትን ለማጠናከር እንደሚረዳም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይም በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች ያለውን ሰላም ለማፅናት የተዘጋጀ ሰነድ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ እየቀረበ ይገኛል።
ከሰዓት በኋላ የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለምና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ስለ ፎረሙ አስፈላጊነት ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ የሁለቱ ክልል ህዝቦች የሰላምና የልማት የጋራ ፎረም ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።