ቀጥታ፡

ተለዋዋጭ በሆነው የአየር ንብረት ሳቢያ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በተቀናጀ አግባብ መሰብሰብ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦ተለዋዋጭ በሆነው የአየር ንብረት ሳቢያ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉንም አማራጭ በመጠቀም በተቀናጀ አግባብ መሰብሰብ  እንደሚገባ ተገለጸ። 

የሚሰበሰብ  ሰብል  ከመጠን በላይ እርጥበት ይዞ ጎተራ ውስጥ ማስገባት ለብልሽት ሊዳረግ ስለሚችልም ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ተመልክቷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የዕጽዋትና ሆርቲካልቸር ትምህርት ቤት የአግሮኖሚ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መንገሻ ከበደ፤ የሰብል አሰባሰብ ሂደት በተቀናጀ መንገድ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት  የአየር ንብረቱ ከተለዋዋጭነቱ የተነሳ ተገማች አለመሆኑ አንስተው፤ ይህም በምርት አሰባሰብ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ሁሉንም ዓይነት አማራጭ በመጠቀም የደረሰ ሰብልን የመሰብሰቡ ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ  ባህላዊና ዘመናዊ ዘዴን በመጠቀም የአርሶ አደሩ እህል በአግባቡ እንዲሰበሰብ ማገዝ  ይገባል ነው ያሉት።

በአገሪቱ ምርት በአግባቡ ባለመሰብሰብ እስከ 26 በመቶ ብክነት እንደሚያጋጥም በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን አንስተዋል።

"በተለይም ሰፋፊ መሬቶች ላይ የለሙ ሰብሎች ባሉባቸው አካባቢዎች ኮምባይነርና መሰል ማሽነሪዎችን በመጠቀም ተገቢ በመሆኑ ለዚህ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ላይ ማተኮር ይገባል" ብለዋል።


 

ለዚህም ማሽኖቹ የሚገቡባቸውን መንገዶች ማስተካከል እንዲሁም ብልሽት ቢያጋጥማቸው በቦታው ቶሎ ጥገና የሚያገኙበትና ሳይቆሙ ስራቸውን እንዲያከናወኑ ነዳጅ የማግኘት ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለበት  ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በተለያዩ አከባቢዎች እየጣለ ያለው ዝናብና እርጥበት መልካም ጎን እንዳለው ያመለከቱት ዶክተር መንገሻ፤ ለከብቶች መኖና የመስኖ ልማትን ለመደገፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በዚህ ሁሉ የግብርና ባለሙያዎች በየዕለቱ የሜቲሮሎጂ የትንበያ መረጃዎችን እየተከታተሉ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግና የማንቃት ስራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሴክተሮች በሰብል አሰባሰብ ላይ እንዲሳተፉና አርሶ አደሩን እንዲያግዙ የመቀስቀስ ስራ ማከናወን እንደሚገባም አንስተዋል።

የተሰበሰበው ሰብል ከመጠን በላይ እርጥበት ይዞ ጎተራ ውስጥ ገብቶ ለብልሽት እንዳይዳረግ አርሶ አደሩ በባህላዊ ዘዴን ተጠቅሞ በማከማቸት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ምሁሩ መክረዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ  የኢትዮጵያ ሜቲሮሎጂ ኢንስቲትዩት ይፋ ያደረገው የትንበያ መረጃ እንደሚመለክተው፤ ከደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ ደጋማ ሥፍራዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ቀጣይነት ይኖረዋል።

ይህን ተከትሎ በሐረሚያ ዩኒቨርሲቲ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን፤  በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለው ቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ ለመስኖ ልማት በተዘጋጁ ችግኞች በተለይም እድገታቸውን ላልጨረሱ፣ ፍሬ በመሙላት ላይ የሚገኙ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት የሚኖረውን ቅዝቃዜ ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም