ቀጥታ፡

በመዲናዋ ባለፉት ወራት በከተማ ግብርና የሚሳተፉ ከ50 ሺህ በላይ አዳዲስ ተጠቃሚዎች ወደ ልማት ገብተዋል -ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦ በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት በከተማ ግብርና ከ50 ሺህ በላይ አዳዲስ ተጠቃሚዎች ወደ ልማት መግባታቸውን የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ለኢዜአ እንደገለጹት የከተማ ግብርና በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የኑሮ ውድነትን በማረጋጋትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስገኘ ነው።

በኅብረተሰቡ ዘንድ በትንሽ ሥፍራ የከተማ ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ ከራስ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ መሆን እንደሚቻል የአስተሳሰብ ለውጥ መፈጠሩንም ነው የተናገሩት።


 

በመዲናዋ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ልማት ዘርፍ በርካታ ተጠቃሚዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮ፣ በወተት ላም እርባታ፣ በንብ ማነብና ሌሎችም ዘርፎች 235 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጸው፤ እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ወደ ልማት ገብተዋል ነው ያሉት። 

የከተማ ግብርናን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የመንግስትና የግል ተቋማት የተቀናጀ የከተማ ግብርናን እንዲተገብሩ እየተደረገ ሲሆን፤ በርካታ የስራ እድልም እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የመዲናዋን የግብርና ምርት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም፤ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ችግር ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ ቁጥር 64/2011 የተመሰረተ ተቋም ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም