የንግድ ስራ ፈቃድ ለሚያድሱ ተገልጋዮች አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት እንደሚችሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2016(ኢዜአ)፦ የንግድ ስራ ፈቃድ ለሚያድሱ ተገልጋዮች ከሰኞ እስከ እሁድ ባሉት የስራ ሰዓት አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት እንደሚችሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በክልሎች ሲሠጡ የነበሩ የአስመጪነት እና የላኪነት የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አገልግሎቶች እንደ ቀድሞው ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መመለሳቸውን የንግድ ስርዓት እና ላይሰንሲንግ ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ጅራታ ነመራ ገልፀዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ በሚኒስቴሩ የሚሠጡ የንግድ ስራ መደቦች ላይ በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የንግድ ስራ ፈቃድ ለሚያድሱ ተገልጋዮች፤ ከሰኞ እስከ እሁድ በመንግስት የስራ ሰዓት የፈቃድ ዕድሳት አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት እንደሚችሉ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 105 ሺህ የንግድ ስራ ፈቃድ ዕድሳት አገልግሎቶችን ለመስጠት መታቀዱን መሪ ስራ አስፈፃሚው ገልፀው፤ ዕቅዱን ለማሳካት እና ቀልጣፍ አገልግሎትን ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ወቅቱ የዕድሳት አገልግሎት የሚሰጥበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በመጨረሻ ቀናት የሚከሰቱ የሲስተም ወረፋዎችን ለማስቀረት እንዲቻል ተገልጋዮች የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች በሟሟላት የንግድ ስራ ፈቃዳቸውን በቀሩት ቀናት አስቀድመው በኦን ላይን እንዲያድሱ መሪ ስራ አስፈፃሚው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም