የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቀጣናውን የጋራ የመበልጸግ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ነው - ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቀጣናውን የጋራ የመበልጸግ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ነው - ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አካባቢውን በተሟላ መልኩ በትብብር ለማበልፀግ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላት ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ላይ ያተኮረ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ያዘጋጁት አውደ ጥናት በሰመራ ተካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ ጉዳዩን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሣሙኤል ክፍሌ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ መልማት መርህን የተከተለ መሆኑን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ከባህር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ሰፊ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በተለይም ከቀይ ባህር ጋር በተለየ ሁኔታ የተቆራኘ ታሪክ ያላት መሆኗን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ የታሪክ እጥፋቶች ምክንያት ትልቅ ሕዝብ ያላት ሀገር ከአዋሽ ውጭ ሁሉም ወንዞቿ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሄዱባት ሀገር የባህር በር አለመኖሯን በቁጭት አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ወንዞች ጎረቤት ሀገራት እየተጠቀሙ ኢትዮጵያን ከባህር በር ማግለል ፍትሃዊ አይደለም ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ የኢትዮጵያ ጥያቄ በአግባቡ ሊጤን እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አካባቢውን በተሟላ አግባብ በትብብር ለማበልፀግ ምቹ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ጥያቄው የጋራ ልማትን ማዕከል ያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላሟና ብልጽግናዋ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመበልፀግ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ሊደግፉ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ምሁራንም ይህንን አጀንዳ ወደ ፊት መግፋት አለባቸው ነው ያሉት።
በተለይም በጉዳዩ ጥናትና ምርምር በማድረግ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን መንገዶች በማመላከት የበኩላቸውን መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህንን ማድረግ የሞራል ግዴታ ተጥሎባቸዋል ብለዋል።
ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በጋራ የመልማት ፍላጎት የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስገንዘብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።