ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ በአደረባት ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች - ኢዜአ አማርኛ
ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ በአደረባት ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች
አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 15/2016(ኢዜአ)፦ አንጋፋዋ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ አይናለም ባልቻ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።
የቀብር ሥነ-ሥርዓቷ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት በቤቴል ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይፈፀማል።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም ላይ ሰፊ አገልግሎት ከሰጡ እና ተፅዕኗቸው ከላቀ ጋዜጠኞች አንዷ የነበረችው ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ በ55 ዓመቷ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
ጋዜጠኛዋ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለ25 ዓመት ያህል ያገለገለች ሲሆን የተለያዩ ክፍሎች እና በተለይም በሕፃናት ፕሮግራም ክፍል ላይ ከ15 ዓመት በላይ መስራቷን ከኢቢሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በከፍተኛ የሥራ ፍቅር እና ትጋት የምትሠራ መሆኗ ባልደረቦቿ የሚመሰክሩላት ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ በጤና እክል ምክንያት ለረጅም ዓመት ከሥራዋ ተገልላም ነበር።
ጋዜጠኛ ዓይናለም የአንዲት ሴት ልጅ እናት እና የሁለት የልጅ ልጆች አያት ነበረች።
ኢዜአ በጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ ኅልፈት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቿና ወዳጆቿ መጽናናትን ይመኛል።