በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ
ደብረብርሀን፤ ታህሳስ 14/2016(ኢዜአ) -ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖች 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት 375 ኩንታል ዱቄት ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉን ያደረጉት በላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን እና ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆናቸው ተመላክቷል።
የደብር ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ በከተማው በፀጥታ ችግር ምክንያት ቁጥራቸው አስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃይ ወገኖች ይገኛሉ።
ቀደም ሲል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ህብረተሰቡ ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ ወገኖች በተለያዩ አካላት የሚደረገው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው፣ ተፈናቃዮች ወደቀድሞ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው ሁሉም ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽንና የወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ለተፈናቃይ ወገኖች በፍትሃዊነት እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል።
የበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ እንግዳው በበኩላቸው፤ ፋውንዴሽኑ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ እንደአገር ለሚከናወኑ ሜጋ ፕሮጀከቶችም ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ከበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽንና ከወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተገኘ 3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ 375 ኩንታል የምግብ ዱቄት ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚው አቶ ይርጋ ዘገየ እንደገለጹት፤ በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ኑሯቸውን እየመሩ ነው።
ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ የእለት ችግራቸውን እንደሚያቃልለው ገልጸው፣ "መንግስት ከእለት ተዕለት ድጋፍ ወጥተን ሰርተን መኖር የምንችልበትን ሁኔታ ሊያመቻችልን ይገባል" ሲሉ ጠይቀዋል።
ወይዘሮ ሩቂያ አህመድ በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ ለወቅታዊ ችግራቸው ማቃለያ እንደሚሆን ተናግረዋል።