የባህር በር አስፈላጊነት በመርከበኛው እይታ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር አስፈላጊነት በመርከበኛው እይታ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 14/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ጭምር ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ጎረቤት አገራት ጉዳዩን አጀንዳቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት የሁለት ወደብ ባለቤት እንደነበረች አስታውሰዋል።
በወቅቱ የነበራት የሕዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚያዊ እድገት አነስተኛ እንደነበር በማስረዳት፤ ዛሬ ላይ የሕዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ በብዙ እጥፍ ቢያድግም የባህር በር የላትም ብለዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሀገራትና መላው ዓለም የኢትዮጵያን እውነተኛ ችግሮችና ፍላጎት መረዳት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአገሪቱን ፈጣን የልማት እንቅስቃሴና ዘላቂ የእድገት ደረጃን ታሳቢ በማድረግ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አገራዊ የጋራ አጀንዳ ሆኗል።
የኢትዮጵያዊያን የጋራ አጀንዳ የሆነውን የባህር በር ጉዳይ በተመለከተ ኢዜአ ለ31 ዓመታት በመርከበኝነት ሙያ አገራቸውን ካገለገሉት ካፒቴን ተፈራ በዳሳ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ካፒቴን ተፈራ የባህር ላይ ሥራ በዓለም ላይ ሰፋፊ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከወኑበትና ለኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስታዋጽዖ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ባህርና የባህር አገልግሎቶችን በመጠቀም ምሳሌ ከሆኑ አገራት መካከል ሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ፊሊፒንስና ሕንድ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
የእነዚህ አገራት የእድገት መነሻ የባህር ላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መሆኑንም ጥናቶችን አጣቅሰው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ከሌላቸው አገራት ተርታ ብትመደብም በታሪክ የባህር በር ያላት አገር እንደነበረች አስታውሰዋል።
ባሳለፉት የመርከበኝነት ሙያ ዘመናቸው ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በምትጠቀምበት ወቅት አገልግሎቱ አላስፈላጊ ወጪን የሚቆጥብና ለብዙዎች የሥራ እድል የፈጠረ እንደነበር ተናግረዋል።
በማደግ ላይ ያሉ አገራት የባህር ላይ የንግድ አንቅስቃሴያቸው በአንድ በኩል የታጠረ መሆን የለበትም የሚሉት ካፒቴኑ አማራጭ ወደቦችን ማስፋትና መጠቀም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያም አሁን በስፋት እየተጠቀመችበት ካለው የጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ አማራጭ ወደቦችን ማስፋትና ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስተዋል።
የባህር በር መርከብን ከቦታ ወደ ቦታ በማጓጓዝ የንግድ ሥርዓትን ከማሳለጥ በዘለለ ከአገራት ጋር የሚፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በአጅጉ የሚያግዝ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ ለአገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራትም ጭምር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህን የኢትዮጵያን ፍላጎት የባህር በር ያላቸውም የሌላቸውም የቀጣናው አገራት አብሮ በማደግ እሳቤ አጀንዳቸው ሊያደረጉት እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።