የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን የልማት አቅም አድርጎ ለመጠቀም ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው - አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን የልማት አቅም አድርጎ ለመጠቀም ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው - አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2016(ኢዜአ)፡- የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን የልማት አቅም አድርጎ ለመጠቀም ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ትላንት መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ በሁሉም ማዕዘናት አያሌ የተፈጥሮ ኃብትና ጸጋ የተቸራት መሆኗን ተናግረዋል።
እነዚህ ጸጋዎች ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ብልጽግና ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ ኃብቶችን በመለየትና በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ቱሪዝም ከሌሎች የልማት ዘርፎች ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በመስኩ የሚከናወኑ ተግባራት ብዙ ፋይዳ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ በአካባቢው ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ኃብትና ጸጋ ገልጦ ያሳየ ነው ብለዋል።
ይህም የተፈጥሮ ኃብትና ጸጋን የልማት አቅም አድርገን ለመጠቀም ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም ወደ ልማት ለመቀየር የሚሰሩ ሥራዎች የሁሉንም የተባበረ አቅም የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም ከፋፋይ ከሆኑ ጉዳዮች ይልቅ የጋራ ሰላምና ልማትን በሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ለበጎ ነገሮች እራስን በማዘጋጀትና ለጋራ ልማትና ብልጽግና በመትጋት ነው ብለዋል።
ልዩነቶች ቢኖሩም ከሚነጣጥሉን ይልቅ የሚያስተሳስሩን ብዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ከኛ ተርፈው ለሌሎች የሚበቁ ጸጋዎቻችንን በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም በየአካባቢው ያለውን የሰው ኃይል አቅም አቀናጅቶ ሥራዎችን በፍጥነትና በጥራት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ መንግሥት በፕሮጀክት አፈጻጸም እያሳየ ያለው ውጤታማ ሥራ በተሞክሮነት ሊወሰድ እንደሚችል አንስተዋል።
ሀገርን ለማስከበር እንደምንረባረብ ሁሉ ሀገርን ለመለወጥና ድኅነትን ለማሸነፍም በጋራ መሰለፍ አለብን ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።