ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2016(ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ትላንተ መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ ኢትዮጵያ ብዙ አቅም ቢኖራትም ወደ ልማት መለወጥ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም በየአከባቢው ያሉ አቅሞችን በአግባቡ አይቶ፣ አቅሞችን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋግጥ አኳያ የአመራር ውስንነት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የመሪዎች የኃሳብ አመንጪነት እንዲሁም የማስፈጸም አቅም አናሳ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመፈጠሩን ተከትሎ በሚነሱ ግጭቶች የሚመጣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጸጋዎችን ለመጠቀም አዳጋች እንደነበር አንስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲም በሀገሪቱ በተለያዩ ሥፍራዎች ያሉ አቅሞችን አሟጦ ለመጠቀም አመራሩ ሚናውን እንዲወጣ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኃሳብ አመንጪነት ትላንት የተመረቀው የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ሀገሪቱ ያሏትን እምቅ አቅሞች እንድትጠቀም በተለይም በሀገራዊ ምክክሩ አማካኝነት ልዩነቶች እንዲፈቱ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የኃሳብ ኃይል ምን ያክል ወሳኝ እንደሆነ ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ትልቅ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲሁም በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዴት ማጠናቀቅ እንደሚቻል የፕሮጀክት አመራር ጥበብን የተማርንባቸው ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ሕዝቡን በሁሉም ደረጃ በማሳተፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነትና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ የታያዙ ውጥኖች እውን እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ የአገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመራቸውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።