ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው መጥተው ልምድና ክህሎታቸውን ማካፈል አለባቸው - ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው መጥተው ልምድና ክህሎታቸውን ማካፈል አለባቸው - ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 13/2016 (ኢዜአ)፦ የዳያስፖራ አባላቶች ወደ አገራቸው መጥተው ልምድና ክህሎታቸውን ማካፈል አለባቸው ሲል እውቁ ዓለም አቀፊ ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅን መርቀው ከፍተዋል።
በዚሁ ጊዜ የተገኘው እውቁ ዓለም አቀፍ ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን፤ የተሰራው ሎጅና በአካባቢው ያለው የተፈጥሮ ኃብት እጅግ የሚደንቅ መሆኑን ተናግሯል።
በአካባቢው ያለው መልክዓ-ምደር፣ የእንስሳት ኃብት እንዲሁም ሌሎች የሕዝቡ ባህል ለአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ ኃብት እንደሚሆን ነው የገለጸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለቱሪስት መዳረሻነት የሚውሉ በርካታ ሥፍራዎች መኖራቸውን ገልጾ እነዚህን ሥፍራዎች ይበልጥ አልምቶ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁሟል።
ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን የኢትዮጵያ የዳያስፖራ አባላት በውጭ አገራት ኢትዮጵያን ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ተናግሯል።
አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የዳያስፖራው አባላት ወደ አገራቸው በመምጣት ያላቸውን ልምድና ክህሎት ማካፈል አለባቸው ብሏል።
የሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን ባለቤት ማያ ኃይሌ በበኩሏ፤ የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ የሚገኝበት ሥፍራና እንዲሁም የተሰራው ሎጅ ሳቢ መሆኑን ገልጻለች።
የዳያስፖራው አባላት አሁን ላይ ወደ አገራቸው መጥተው ለአገራቸው እድገት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብላለች።
ለዚህም እርሷም የበኩሏን እንደምታደርግ ነው ያረጋገጠችው።