እንደ ኮይሻ ያሉ ሥፍራዎችን መጎብኘት ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅ ይረዳል - አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ - ኢዜአ አማርኛ
እንደ ኮይሻ ያሉ ሥፍራዎችን መጎብኘት ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅ ይረዳል - አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2016 (ኢዜአ)፡- እንደ ኮይሻ ያሉ ሥፍራዎችን መጎብኘት ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅ ይረዳል ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የገበታ ለሀገር የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ እንደ ኮይሻ ያሉ ሥፍራዎችን መጎብኘት ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅ ይረዳል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ የቱሪዝም እምቅ ኃብት ያላት ሀገር በመሆኗ በቀጣይ ዓመታት ከቀዳሚ የጎብኚዎች መዳረሻ አገራት አንዷ እንደምትሆን ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ ጀምሮ በርካታ ሥፍራዎችን ለመመልከት እየሞከርኩኝ ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ አካባቢዎች መሄዳቸውን ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ኮይሻ ያሉ ሥፍራዎችን መጎብኘት ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅና ለመረዳት ያስችላል ብለዋል አምባሳደር ኧርቭን።
ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ጀምሮ የቱሪስት መስህቦችን ሲመለከቱ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ፓርኩ ልብን የሚማርክና የሚመስጥ የተፈጥሮ ጸጋ የተላበሰ መሆኑን ማየት ችያለው ብለዋል።
ቱሪዝምን ባህልንና ሌሎች ጸጋዎችን ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው የሀገሪቱን ብዝሃ ኢኮኖሚ ውጥን እውን ለማድረግም ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።
በቀጣዮቹ ዓመታት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ይበልጥ እንደሚያድግ አመለካቾች መኖራቸውን ጠቁመው ኢትዮጵያ የቱሪዝም እምቅ ኃብት ያላት ሀገር በመሆኗ በቀጣይ ከቀዳሚ መዳረሻዎች አንዷ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለው ብለዋል።
በሌላ በኩል አሜሪካና ኢትዮጵያ በትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው አጋርነቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተለይም በእርሳቸው የአምባሳደርነት ዘመን ይህንን እውን ለማድረግ እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።