በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል
ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 13/2016 (ኢዜአ)፡- ስራ ፈጣሪ የሰው ሀይል በማፍራት በኩል የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ትኩረት መሰጠቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው የ2016 በጀት ዓመት ያለፉት የአምስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በዱራሜ ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ይርጋ ሃንዲሶ እንዳሉት፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ ስራ ፈጣሪዎችን ከማፍራት አንጻር ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው።
በዚህም ከስራ ጠባቂነት አመለካከት የወጡና ስራ ፈጥረው ለሌሎች መትረፍ የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት ያለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል አቅማቸውን ከማዳበር ጀምሮ ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
በክልሉ በሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት አዳዲስ የኢንደስትሪ ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለማህበረሰብና ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ማሸጋገር የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።
ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው በቂ እውቀትና ክህሎት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በዚህም በጥራትና በዋጋ በተሻለ መልኩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችልና ተወዳዳሪነትን ግቡ ያደረገ ስልጠና ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመላክተዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ በክልሉ በሚገኙ 37 ፖሊና ኢንዱስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጆች ስልጠናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ 30 ሺህ በላይ ሰልጣኞች ፈጠራ ላይ እንዲያተኩሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ አጭሶ በበኩላቸው፤ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ያላቸው ቢሆንም ስራ ላይ እንዲውሉ ከማድረግ አንጻር ውስንነት እንዳለ ጠቁመዋል።
ይህም ሆኖ በዞኑ በሚገኙ 13 መዋቅሮች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ብልሽት ሲያጋጥም የዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ጥገናውን ስለሚያካሂድ የጊዜና ተጨማሪ ወጪዎች እያዳነ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ለዞኑ ከፍተኛ የሆነ እፎይታ የሰጠ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ሌሎችንም በማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።
የዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ደሳለኝ አኔ እንዳሉት፤ኮሌጁ ከስራ ጠባቂነት አመለካከት የወጡና ስራ በመፍጠር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዜጎችን ለማፍራት የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል።
ለዚህም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ማህበራት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማሸጋገርን ጠቅሰዋል።
ስራ ፈጠራንና ዘላቂ ሀገራዊ የውጥ ሂደቱን ለማጠናከር የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሚና አይተኬ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ አወል ሸንጎ ናቸው።
በኮሌጁ በንድፈ ሀሳብና በተግባር ላይ የተመሰረተ የመማር ማስተማር ስራን በማከናወን በእውቀትና ክህሎት ተቋሙ የበለፀጉ ዜጎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ ከአካባቢ አልፎ ለሀገር የሚበቁ ዜጎችን ለማፍራት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የተቋም አቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሰልጣኝ ቅበላ ላይ ትኩረቱን ባደረገው መድረክ ላይ በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የተቋማቱ መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ።