ቀጥታ፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከተመረጡ 14 ኢንዱስትሪዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2016 (ኢዜአ)፡- የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማቅረብ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከ14 ኢንዱስትሪዎች ጋር ተፈራረመ። 

ሥምምነቱን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ ከኢንዱስትሪ ሥራ መሪዎችና ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።


 

ሥምምነቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራትና አገሪቱ በዘርፉ የጀመረችውን እድገት ለማስቀጠል ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል።  

በሥምምነቱ ኢንዱስትሪዎች ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር በሚፈልጉት የትምህርት መርኃ- ግብር የሰው ኃይል ለማሰልጠን እንደሚያስችላቸው ተገልጿል። 

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በከፍተኛ ትምህርት የተደረገውን ሪፎርም ተከትሎ  ዩኒቨርሲቲው የተግባር ዩኒቨርሲቲ ሆኗል ብለዋል።


 

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ከጽንሰ-ኃሳብ በተጨማሪ በተግባር የተደገፈ ትምህርት መስጠት ይጠበቅበታል፤ ለዚህም ደግሞ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ ናቸው ነው ያሉት።  

ለተግባር ልምምድ ኢንዱስትሪዎች ሁነኛ መዳረሻ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት ይህንን በማሳለጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል። 

ጎን ለጎንም ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲሁም የኢንዱስትሪውን የሰው ኃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመሙላት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል። 

የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር የሚቀርፍ ነው ብለዋል።  


 

በትምህርት ሴክተሩ እየተደረጉ ካሉ ሪፎርሞች መካከል አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተልዕኮ ልየታ  ነው ያሉት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርቶችና ፕሮግራሞች ዴስክ ኃላፊ ተስፋዬ ነገዎ ናቸው። 

ሥምምነቱ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተሰጠውን ሚና በአግባቡ ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ እንዲፋጠን እንደሚያደርግለት ተናግረዋል። 

ሥምምነቱ ዩኒቨርሲቲውን ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎችንም በዘርፉ የተመረቀ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ ለማግኘት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

ለሥምምነቱ ተግባራዊነት ትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም