በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ የባለድርሻ አካላት ምላሽ አበረታች ነው- ኮሚሽኑ

ባህር ዳር ፤ ታህሳሰ 13/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ የባለድርሻ አካላት ምላሽ አበረታች መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

በቢሮ ሃላፊ ማዕረግ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋው ባታብል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዝናብ እጥረት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ በዋግ ኽምራና ሰሜን ወሎና ሌሎች ዞኖች ድርቅ ተከስቷል። 

በዚህም ከሌሎች አካባቢዎች በግጭት ተፈናቅለው የመጡትን ከ608 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ህዝብ የአስቸኳይ ምግብ እህል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር በተደረገ ጥረት በክልሉ መንግስትና እንደ ንጋት ባሉ የልማት ድርጅቶች አማካኝነት 27 ሺህ 470 ኩንታል የምግብ እህል ወደ ዞኖቹ በመላክ መሰራጨቱን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም የፌዴራል መንግስት 277 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብና 120 ሺህ 867 ኩንታል የምግብ እህል በመመደብ ተጎጅዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመዋል። 

ከምግብ እህሉ ውስጥ 69 በመቶ የሚሆነው ወደ ክልሉ ገብቶ ለየዞኖቹ መላኩንና ጥሬ ገንዘቡ ለወረዳዎች መድረሱን ጠቁመው፤ ቀሪው "በቅርቡ እንደገባ የሚላክ ይሆናል" ብለዋል።  

በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና አንዳንድ ድርጅቶችም በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ የበኩላቸውን ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

በሁለተኛው ዙር የምግብ እህል አቅርቦትን ለማሳካትም የክልሉ መንግስት 200 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመው፤ የፌዴራል መንግስትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የምግብ እህል ለማቅረብ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል መቀዛቀዝ ታይቶባቸው የነበሩት ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም አሁን ላይ ለ390 ሺህ ህዝብ የምግብ እህል ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ፀደይ፣ አባይና አማራ ባንኮች ገንዘብ በመመደብ በአመልድ ኢትዮጵያ በኩል እህል በመግዛት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም በድጋፉ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። 

የባለድርሻ አካላት እያሳዩት ያለው ምላሽ የሚበረታታ መሆኑን አመልክተው፤ በአካባቢው ድጋፉ በፍጥነት እንዲደርስ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ህብረተሰቡ የእርዳታ እህል የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን ጠብቆ በማሳለፍ ከተጎጅዎች ጎን መቆማቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የ09 አቅኝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማኑዔል አስፋው እንዳሉት፤ በዝናብ እጥረት የዘሩት ሰብል ደርቆ በመቅረቱ ቤተሰቦቻቸው ለችግር ተጋልጠዋል።

መንግስት ባደረገላቸው 14ሺህ  ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ እህል ሸምተው ጊዜያዊ ችግራቸውን ማቃለላቸውን ጠቁመው፤ ማምረት እስኪችሉ ድረስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የዚሁ ቀበሌ  አርሶ አደር ሙሉቀን አበበ በበኩላቸው፤ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ባለፈ እንስሳቱ ለችግር እንደተጋለጡ ገልጸዋል።

መንግስት የአንድ ወር ቀለብ የሚሆን የምግብ እህል ድጋፍ በማድረጉ የእለት ችግራቸውን ማቃለላቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይነት ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲቀርብላቸውም አመልክተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም