ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደብ ጥያቄ ቅንጦት ሳይሆን ሞራላዊና ህጋዊ ተገቢነት ያለው ነው - ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደብ የማግኘት ጥያቄ ቅንጦት ሳይሆን ከዓለም አቀፍ ንግድና የኢኮኖሚ መርህ አንፃር ሞራላዊና ህጋዊ ተገቢነት ያለው መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል ገለጹ።

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ፣ ከመቀሌ፣ ከድሬዳዋና ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ያላት ስትራቴጃክ ፍላጎት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል፤ ወደብና ኢኮኖሚ፥ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ፍላጎት በሚል መወያያ ፅሑፍ አቅርበዋል።

በዘመኑ የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሎጂስቲክስና የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም ወደብ የዓለም ንግድን የሚያሳልጥ ቁልፍ መሣሪያ ነው ያሉት ዶክተር አጥናፉ፤ የባህር በር ሀገራት በዓለም አቀፋዊ ንግድ ውስጥ እንዲሳተፉና የኢኮኖሚ እድገታቸውን እንዲያረጋግጡ አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።

አፍሪካዊያን ከሚቸገሩባቸው የንግድ እንቅፋቶች አንዱ የባህር በር ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል ዶክተር አጥናፉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 80 በመቶ የንግድ እቃዎች የሚተላለፉት በወደቦች መሆኑን በመጥቀስ ከዓለም የንግድ ልውውጥ ውጭ በመሆን የሚረጋገጥ ዕድገት እንደሌለም አንስተዋል።

ተመራማሪው አክለውም 90 በመቶ የዓለም ንግድ የሚጓጓዘው በባህር ላይ ነው ብለዋል።

ለዚህም የመርከብ ትራንስፖርት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው መርከቦች የሚጭኑበትና የሚያራግፉበት ዘመናዊ ወደብ መገንባት የግድ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዓለም ህዝብ 17 ነጥብ 8 በመቶ የሚገኝባት አፍሪካ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ድርሻዋ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑም ገልጸዋል።


 

ከዚህም ውስጥ እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርናና የማዕድናት ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

በዓለም ላይ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ካላቸው ሀገራት ዓመታዊ ጥቅል ምርታቸው በአማካይ በ31 በመቶ እንደሚያንስም ገልጸዋል።

የዋጋ ግሽበት ምጣኔያቸው በ26 በመቶ እንደሚጨምር ገልጸው፤ የግብይት ሂደት ጥቅል ወጪያቸው ኢ-መደበኛውን ጨምሮ በዓመታዊ ምርታቸው 70 በመቶ እንደሚይዝ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የንግድ ውድድር ላይ በገቢና ወጪ ምርት ብቁ ለመሆን ጥራት ያለው ምርት፣ ብቁ አምራች፣ወደብ መገንባትና አካባቢን ማልማት የግድ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ኢኮኖሚ ያለቀጣናዊ ትስስር የዓለም ኢኮኖሚ ያለ ንግድና ኢንቨስትመንት አይሳካም ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ሚዛንን ለማስጠበቅ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ወሳኝ መሆኑንም ዶክተር አጥናፉ አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደብ ጥያቄ ቅንጦት ሳይሆን ሞራላዊና ህጋዊ ተገቢነት እንዳለውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም