ግብርናን የሚያዘምኑ ግብዓቶችን በተቀናጀ መልኩ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው - የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናን የሚያዘምኑ ግብዓቶችን በተቀናጀ መልኩ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው - የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን
ሚዛን አማን ፤ታኅሣሥ 13/2016 (ኢዜአ) ፦የሜካናይዜሽንና ሌሎች ግብርናን የሚያዘምኑ ግብዓቶችን በተቀናጀ መልኩ ለአርሶ አደሮች በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ ።
ኮርፖሬሽኑ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እያስገነባ ያለውን የቦንጋ ግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን ማዕከል በተያዘው በጀት ዓመት በከፊል ሥራ እንደሚያስጀምር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኦፕሬሽናዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ መሠራት አለበት።
ኮርፖሬሽኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ የሜካናይዜሽንና ሌሎች ግብርናን የሚያዘምኑ ግብዓቶችን በተቀናጀ መልኩ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።
ከ411 ሚሊዮን በላይ ብር እየተገነባ ያለው የቦንጋ ግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን ማዕከል በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በ2014 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የተጀመረው የግንባታው የሥራ ሂደት በግብዓት እጥረት ምክንያት በተያዘለት ጊዜ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም በዚህ ዓመት በከፊል በማጠናቀቅ በቦታው ሥራ ለመጀመር ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ባለ አራት ወለል ሕንጻ፣ እያንዳንዳቸው 40 ሺህ ኩንታል የሚይዙ አራት ትላልቅ መጋዝኖች፣ ዘመናዊ የማበጠሪያ ማሽንና ሌሎች የኬሚካልና መሰል ግብዓቶችን የሚይዙ መጋዝኖችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ እንደ ሀገር ካሉ 25 ማዕከላት መካከል ትልቁ የሚባል መሆኑን ገልጸው ሙሉ በሙሉ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለደቡብ ምዕራብ ክልል፣ ለከፊል ኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
"ማዕከሉ ለአካባቢው ካለው አስፈላጊነት የተነሳ ግንባታው በፍጥነት እንዲያልቅ ፕሮጀክቱን ለሁለት ኮንትራክተሮች ከፍሎ በመስጠት ሥራው እንዲፋጠን እየተደረገ ነው" ብለዋል።
በኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር ድርጅት የቦንጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስረስ አስፋው በበኩላቸው ማዕከሉ አልቆ ወደ ሥራ ሲገባ የክልሉን የግብርና ሥራ ከማዘመንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል ።
አሁን ላይ የግንባታ አፈጻጸሙ 80 በመቶ መድረሱንና በቅርበት የመከታተልና የመደገፍ ተግባር እንደ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
"ከሜካናይዜሽንና ሌሎች የእርሻ ግብዓቶች ባሻገር ማዕከሉ በዋናነት ምርጥ ዘርን የሚያከፋፍል ሲሆን የምርጥ ዘር ልማቱ በክልሉ ካፋ ዞን ታማሻሎ 1 ሺህ 70 ሄክታር ላይ እየተመረተ ዘር መስጠት ጀምሯል" ብለዋል።
ከክልሉ መንግስት በተሰጠው 5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በምዕራብ ኦሞ ዞን በቅርቡ የሚጀመረው የኮካ የሰብል ዘር ብዜት እርሻ ጣቢያ ለማዕከሉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
የማዕከሉ መገንባት ከዚህ ቀደም ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን ለማምጣት የሚደረገውን የርቀት ችግር የሚያቃልል እንደሆነም ገልጸዋል።