ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2016(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው።

በዚህም በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጠይቀዋል።

የመጀመሪያ ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ የሚቆይ ሲሆን 'connect to your culture' በሚል የተደረገ ጥሪ ሲሆን፣ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ የዳያስፖራ አባላት የገና በዓልን ጨምሮ ሌሎች በዓላት ላይ እንደሚታደሙ ተናግረዋል።

ሁለተኛው ዙር ደግሞ 'connect to your history' በሚል በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ወቅት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሶስተኛው ዙሩ 'live your legacy' በሚል በኢትዮጵያ ከክረምት ወቅት ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በዚሁ ጊዜ የሚመጡ የዳያስፖራ አባላት ችግኝ መትከልን ጨምሮ በሌሎች ስራዎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢትዮጵያ ሆቴሎች ልዩ የቅናሽ ክፍያ አገልግሎት እንደሚኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም