ለግድቡ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ እስከ ፍጻሜው አጠናክረን እንቀጥላለን - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ለግድቡ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ እስከ ፍጻሜው አጠናክረን እንቀጥላለን - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች
ጂንካ፤ታህሳስ 13 / 2016 (ኢዜአ) ፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ።
በክልሉ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በተደረገው የሀብት ማሰባሰብ ስራ ከ661 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ባለሙያ አቶ አበበ ለገሰ "ግድቡ ከምኮራባቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው" ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን ኩራት ነው ያሉት አቶ አበበ ኢትዮጵያውያን ያለማንም እርዳታ በራሳቸው አቅም ማደግና መበልፀግ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ለአራት ዙር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ባለሙያው "በቀጣይም ለግድቡ ግንባታ የሚጠበቅብኝን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሩህ ተስፋችንን አሻግረን የምናይበት እና ለቀጣዩ ትውልድ ደማቅ አሻራችንን ያኖርንበት ፕሮጀክታችን ነው ያሉት ደግሞ በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ባለሙያ አቶ ምስራቀፀሐይ መሰለ ናቸው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መድረሱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልፀው ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባልደረባ ወይዘሮ መርካታ አለሙ "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበትና አሻራቸውን ያኖሩበት የጋራ ታሪካችንና አኩሪ ድላችን ነው" ብለዋል።
ለህዳሴ ግድብ የማይዘረጋ እጅ የለም ያሉት ወይዘሮ መርካታ በተባበረ ክንድ የጀመረነውን ይህን ታላቅ አሻራ ተባብረን እናጠናቅቀዋለን ነው ያሉት።
ለግድቡ ከደሞዜ ላይ በመቀነስ ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ባልደረባ ወይዘሮ ታደለች በቀለ በበኩላቸው "ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለልጆቼ የማወርሰው ብቸኛው ቅርሴ ነው ይህን ደማቅ ታሪካዊ አሻራ የሰራው ጀግናው ትውልድ አካል በመሆኔም ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል" ብለዋል።
እስካሁን በተደረገው ህዝባዊ ተሳትፎ ለአራት ተከታታይ ዙሮች ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ድጋፍ እንዳደረጉና አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ እስራኤል ለኢዜአ እንደገለፁት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መላው ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ ነጋዴው፣ የመንግስት ሰራተኛው ከልጅ እስከ አዋቂ በአጠቃላይ ሁሉም የክልሉ ህዝብ በሞራልና በገንዘብ ሰፊ ደጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
እስካሁን ለግድብ ግንባታው የክልሉ ህዝብ ከ661 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።
በዚህ አመት በክልሉ 38 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው እስካሁን ከቦንድ ግዢ እና ከሌሎች የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ጠቁመዋል።