መጪው የገና በዓል በላሊበላ በሰላም ለማክበርና ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መጪው የገና በዓል በላሊበላ በሰላም ለማክበርና ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ወልዲያ ፤ ታህሳስ 13 / 2016(ኢዜአ)፡- መጪውን የገና በዓል በላሊበላ በሰላም ለማክበርና ወደ ስፍራው የሚመጡ ጎብኚዎችን በተገቢው ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወንድምነው ወዳጅ እንዳሉት፤ በዓሉን ለማክበር እንግዶች ወደ ላሊበላ ሲመጡ ሊደረግ ስለሚገባው አቀባበል ከህብረተሰቡና ከአስጎብኚ ማህበራት መሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከእንግዶች ቁጥር ጋር የሚመጥን ዝግጅት እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምዕምናኑ የሚገለገልበት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣የህክምና ማዕከልና መሰል አገልግሎቶችን የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንዳለበት ከንቲባው ተናግረዋል።
በዘንድሮው የገና በዓል ከ250 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ ይህም የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የጎላ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀሐይነው ሲሳይ በበኩላቸው፤ መጪውን የገና በዓል በላሊበላ በሰላምና በስኬት እንዲከበር ለማስቻል የተለያዩ አቢይና ንኡሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ መግባታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ተዋቅረው ወደ ስራ ከገቡት ኮሚቴዎች መካከል የህዝብ ግንኙነትና ፕሮሞሽን፣ የሎጀስቲክ፣ የፀጥታና የጤና ዘርፎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በዓሉን ለማክበርና ታሪካዊ ስፍራውን ለመገብኘት ለሚመጡ እንግዶች ተገቢውን እገዛ፣ ድጋፍና እንክብካቤ የሚያደርጉ አስተባባሪዎች መመቻቸታቸውንም ገልጸዋል።
እንዲሁም ሰላምን የሚያስከብሩ ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተባብረው አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ እየተሰናዱ እንደሚገኙ ተመልክቷል።
የውጭም ይሁን የአገር ውስጥ ጎብኝዎችም የገናን በዓል በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ እንዲያከብሩም ጥሪ ቀርቧል።
በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።