ኢትዮጵያን ጨምሮ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የባህር ውሃን ለቀጣናዊ ልማትና ደህንነት ሊያውሉ ይገባል - ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ጨምሮ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የባህር ውሃን ለቀጣናዊ ልማትና ደህንነት ሊያውሉ ይገባል - ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 13/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችንና የባህር ውሃን ለቀጣናዊ ልማትና ለአካባቢው ደህንነት መረጋገጥ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።
ተመራማሪው በሰመራ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ በሚገኘው አውደ ጥናት ላይ ''ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰስና ባህር ረገጥ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ ጂኦፖለቲካና ቀጣናዊ ደህንነት'' በሚል ርዕሰ ጉዳይ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የብዙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተጋሪ መሆንዋን አንስተው፤ የናይል ዋነኛ የውሃ ምንጭ እንደሆነችም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ዘላቂ የሰላም እና የደህንነት ፍላጎት አላት ያሉት ዶክተር ያዕቆብ፤ ለጎረቤቶቿ ሰላምና ልማት በተግባር የምትተጋ መሆኗንም ጠቁመዋል።
የባህር በር የማግኘት ጥያቄው ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም አስከብራ የሌሎችንም ለማስከበር የምትተጋ መሆኗን ማሳየት ይገባልም ነው ያሉት።
ባህር ረገጥ ሀገራት የሚገኙበት ውሃ የአካባቢው ሀገራትና ህዝቦች በጋራ የሚጠቀሙበት፣ የኢኮኖሚ መንቀሳቀሻ እና የጋራ ዕድገት ምንጭ መሆን አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተፋሰሶቿን ስታለማ ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ተሞክሮ በመቀመር የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን ማሳካትም እንደሚገባ አንስተዋል።
የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪና የባህር ውሃን ለቀጣናዊ ልማትና ደህንነት መጠቀም አለባቸው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በየጊዜው ፍላጎቷ እያደገና ለቀጣናዊ ትብብር የሰጠችው ስፍራ ትልቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ ላይ እየገነባቻቸው ያሉ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ መሠረተ ልማቶች ቀጣናዊ የኃይል ቋትና የትስስር ባህር ረገጥና ውሃ አቀባይ ሀገራት ካላቸው የልማት ፍላጎት ጋር ተያያዥ መሆኑ ተናግረዋል።
የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ በአንድነት የመቀጠል እጣ ፈንታቸውን ለማፅናት ትብብርንና የውሃ ሀብትን በጋራ መጠቀምን ማጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሀገራቱ ከትብብር ባለፈም አንዱ ለሌላው ማደግ ሊቆረቆር ይገባል ያሉት ዶክተር ያዕቆብ፤ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ለጋራ ደህንነት ትኩረት መስጠት እንደሚገባም እንዲሁ።
መንግሥት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ለማሰጠት በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ጥርጣሬን በማስወገድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ይፋዊ ውይይትን በመጀመር ለጉዳዩ እልባት የሚሰጥ ግብረ ኃይል ሊያቋቁም ይገባልም ብለዋል።