ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላት ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ትክክለኛ መሆኑን ምሁራን በአግባቡ ማሳየት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላት ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ትክክለኛ መሆኑን ምሁራን በአግባቡ ማሳየት አለባቸው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 13/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝና በቀይ ባህር ላይ ያላት ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ትክክለኛ መሆኑን ምሁራን በአግባቡ ማሳየት እንደሚገባቸው ተገለፀ።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላት ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ላይ ያተኮረ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ያዘጋጁት አውደ ጥናት በሰመራ እየተካሄደ ነው።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሐመድ ኡስማን በዚሁ ጊዜ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አውደ ጥናቱ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ለማሳካት ምሁራን የምርምር አውድ እንዲለዩ የሚያስችል ታሪካዊ ሁነት ነው ብለዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ያላትን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ለማሳካት የታሪክ፣ የጂኦ-ፖለቲካና ዓለም አቀፍ ህግ አማራጮች እንደሚዳሰሱም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚና የህዝብ ትብብር እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስር ርዕይዋን ለማሳካት የባህር በር ማግኘት እንደሚገባት ጠቅሰዋል።
ይህን ስትራቴጃካዊ ፍላጎት ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብሔራዊ ጥቅምን በሚመለከት ዝርዝር ጥናቶችን ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ለቀይ ባህር ከፍተኛ ቅርበት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት መሆኗ ሊያስቆጭ የሚገባ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ሰፊ የልማት ዕድል ያለው ቢሆንም ከፍተኛ አለመረጋጋትና ተለዋዋጭ ሁኔታን እያስተናገደ በመሆኑ ይህን ለመቀየር ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ቀይ ባህር በክፉም በደጉም የኢትዮጵያ የታሪክ አካል መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እውነታውን በመግለጥ ኢትዮጵያና ቀይ ባህርን ከታሪክ፣ ከስልጣኔ፣ ከጂኦ ፖለቲካ አንፃር በጥናት በተደገፈ መንገድ ትክክለኛውን ነገር ማስገንዘብ አለባቸው ነው ያሉት።
የሶፍትፓወር ዲፕሎማሲን ጥቅም ላይ በማዋል የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መሥራት አለባቸውም ብለዋል።
አውደ ጥናቱን ሰመራ፣ አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ጅግጅጋና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ አዘጋጅተውታል።