በአዲስ አበባ ከ 1 ሺህ በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከ 1 ሺህ በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በአንድ ሳምንት በተካሄደ ጥምር ኦፕሬሽን ከ 1 ሺህ በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ሕብረተሰቡን ሲያማርሩ የቆዩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የተቀናጀ ኦፕሬሽን እየተካሄደ እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ነዋሪዎች ያለአንዳች ስጋት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ላይ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ጨምሮ የፌደራልና የአዲስ አበባ የፖሊስ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የኮልፌ፣ የልደታና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ የኦፕሬሽን ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ግርማ ተሰማ፥ የመዲናዋን ነዋሪዎች እያማረሩ የሚገኙ የዝርፊያና ተያያዥ ወንጀሎችን ለመከላከል በጥምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኦፕሬሽኑም በጦር መሳሪያ ጭምር በመታገዝ በቡድን ተደራጅተው ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ በሚከቱ፣ የወንጀል መንስኤ የሚሆኑ፣ የአደንዛዥ ዕጽ፣ ቁማር ቤቶች እና ሌባ ተቀባይ አካላት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
በተሰራ ኦፕሬሽንም የወንጀል መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት በዝርፊያና ልዩ ልዩ ወንጀል የተጠረጠሩ አካላትንና የተዘረፉ ንብረቶችን በቁጥጥር ስራ ማዋላቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው ሳምንት ብቻ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በተሰራ ኦፕሬሽን ሞባይሎች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች በርካታ የተዘረፉ ንብረቶችም ተይዘዋል ብለዋል።
ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ተይዘውም ተገቢው የህግ ማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
ወጣቶችን ወደ አልባሌ እና ወንጀል ድርጊት የሚመሩ ከ6 ሺህ በላይ ህገ-ወጥ የቤቲንግ እና የአደንዛዥ ዕፅ አስጠቃሚ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር በኃይሉ ደጀኔ፤ የሞተር አሽከርካሪዎች በሚፈጽሙት ንጥቂያ ህብረተሰቡን እየተማረረ መሆኑን ጠቁመው፥ በቀጣይም ህጋዊ ሥርዓት ብቻ በመከተል ስራቸውን ማከናወን እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ውጤታማ የወንጀል መከላከል ስራ በመሰራቱ በርካታ የተዘረፉ ንብረቶችና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል የመዲናዋ ነዋሪዎችም ያለአንዳች የጸጥታ ስጋት የሚንቀሳቀሱበት ምኅዳር እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰለሞን ፈንታሁን፥ የሞባይል ንጥቂያ፣ የሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እና የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ስርቆት ነዋሪዎችን እያማረሩ ነው ብለዋል።
ኦፕሬሽኑ በቡድን ተደራጅተው ወንጀል በሚፈጽሙ እና የተሰረቁ ንብረቶችን በሚቀበሉ እንዲሁም በአደንዛዥ ዕፅ አስጠቃሚዎችና በቁማር ቤቶች ላይ መካሄዱ ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎቹ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ፖሊስ እየወሰደ በሚገኘው ኦፕሬሽን ሂደት ውስጥ መረጃ በመስጠትና በመጠቆም እገዛ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርበዋል።