ቀጥታ፡

የባህር በርን በማግኘት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጡ ረገድ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው

አርባ ምንጭ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ) ፦ የባህር በርን በማግኘት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አስከብሮ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ የምሁራን ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄን በተመለከተ “የባህር በር የልማት በር” በሚል መሪ ሃሳብ የምሁራን ውይይት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ የባህር በርን በማግኘት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በአሁኑ ጊዜ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው የኢትዮጵያ የባህር በርን የማግኘት ጥያቄ ይህንን የሚያጠናክርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀገራችን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ምሁራን ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብና ግንዛቤ በመፍጠሩ ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡


 

በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ታሪኳ ወልደመድህን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ባለመሆኗ  ከሀገር የሚወጡና ወደ ሀገር የሚገቡ ዕቃዎችን ለማሳለፍ ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል መገደዷን ገልጸዋል፡፡

የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ኢትዮጵያ ያላትን ህዝብና የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃን በአግባቡ ለማስተናገድ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባህር በር በተለይ እንደ ዓለም የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ከማረጋጋትም በላይ የሀገራችንን ዕድገት ለማፋጠን ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

የባህር በርና የወደብ አጠቃቀም ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጥያቄ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ታሪኳ ለዚሁም ዩኒቨርሲቲው የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩም ሆነ ለመላው አፍሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት የስበት ማዕከል ናት ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህርና ጥናት አቅራቢ አቶ ዓባይ ወርቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት፣ የአፍሪካ ህብረት መስራች፣ እንዲሁም ወደ ተለያዩ ሀገራት የሰላም አስከባሪዎችን በመላክ ጠንካራ ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰዋል።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ትስስር እየፈጠረች መሆኗን ጠቅሰው፤ ''ይህም ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም እንዳላት የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡

የሀገራችን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የልማት ፍላጎት ከህዝብ ቁጥሯ ጋር እየጨመረ በመምጣቱ የራሷ የባህር በር ባለቤት በመሆን የተሳለጠ የባህር ትራንስፖርትና የሎጂስትክስ ሲስተምን መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም ህዝቡ የውስጥ አንድነቱን በማጠናከር በአጀንዳው ዙሪያ አንድ በመሆን ለመጪው ትውልድ ጠንካራ ሀገርን ለማስረከብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም