ማዕከሉ የማር ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እያፈለቀ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ የማር ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እያፈለቀ መሆኑን አስታወቀ
ሰቆጣ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የማር ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
ማዕከሉ በእንስሳት ምርምር ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ያለመ ጉብኝት አካሂዷል።
የምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነ ባህሩ በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት፣ የዞኑ አየር ንብረት እና ስነ ምህዳር ጥራት ያለው ነጭና ቀይ ማር ለማምረት ተመራጭ ነው።
ማዕከሉም የማር ምርታማነትን በማሳደግ በዘርፉ የተሰማሩትን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ ሥራ በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተፋሰስ የለማ በ57 ሄክታር መሬት የደን ሃብት ላይ ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የንብ ማነብ እና የምርምር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በተፋሰሱ ላይ ለንቦች ተስማሚ የሆኑ እፅዋትን በመለየት፣ በማባዛትና በማልማት በሰርቶ ማሳያነት ለአርሶ አደሩ መማሪያ ማድረጉን ተናግረዋል።
ህብረ ንብን እንዴት ማብዛት እንደሚቻል በተመራማሪዎች በኩል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም ለመድሃኒትነት ተመራጭ የሆነውን የጣዝማ ማር በዘመናዊ መልኩ ለማምረት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በተሰሩ ሥራዎችም በባህላዊ ቀፎ ይገኝ የነበረውን ከ15 ኪሎ ግራም ያልበለጠ የማር ምርት ዘመናዊ ቀፎና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እስከ 35 ኪሎ ግራም ለማግኘት ተችሏል ብለዋል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን እንዳሉት ማዕከሉ የሰብል፣ የእንስሳት እና የማር ምርታማነትን ለማሳደግ አበረታች ሥራ እየሰራ ነው።
አርሶ አደሩን በመደገፍና በማበረታታት የንብ ማነብ ሥራን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ ቀፎ በማሸጋገርና የማር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል መልካም ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
"በማዕከሉ በቴክኖሎጂና በአዳዲስ አሰራር የተደገፈ የንብ ማነብ ስራን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል" ያሉት ደግሞ የዞኑ የእንስሳት ሃብት ልማት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሲሳይ አያሌው ናቸው።
አርሶ አደሮች በንቦች ተፈላጊ የሆኑ እጽዋትን በማልማትና የህብረ ንብ ቁጥርን በማብዛት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረውን ምርምር ዳር እንዲደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የምርምር ማዕከሉ በዞኑ ያሉ ሦስት ወረዳዎች ላይ 22 አናቢዎችን በማሳተፍ እያካሄደ ያለውን የምርምር ተግባር በቀጣይ ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች የማስፋት ሥራ እንዲሰራም ጠይቀዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የምርምር ማዕከሉ ተመራማሪዎችን ጨምሮ የብሔረሰብ አስተዳደሩ የግብርና አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።