በአዲስ አበባ ከ1 ሺህ በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከ1 ሺህ በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በአንድ ሳምንት በተካሄደ ጥምር ኦፕሬሽን ከ1 ሺህ በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ሕብረተሰቡን ሲያማርሩ የቆዩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የተቀናጀ ኦፕሬሽን መካሄዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
በተያዘው ሳምንት የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በሰሩት ጥምር ኦፕሬሽን ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ተገቢው የማጣራት ሥራ እየተሰራ ነው።
ልዩ ኦፕሬሽኑን የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በጥምረት ማካሄዳቸው ነው የተገለፀው።
ኦፕሬሽኑ በቡድን ተደራጅተው ወንጀል በሚፈጽሙ እና የሌባ ንብረቶችን በሚቀበሉ እንዲሁም በአደንዛዥ ዕፅ አስጠቃሚዎችና በቁማር ቤቶች ላይ መካሄዱ ተገልጿል።
በኦፕሬሽኑ ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ በዚህም በርካታ የተሰረቁ የሞባይል ስልኮች፣ ላፕቶፖች፣ የጦር መሳሪያዎች እና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ንብረቶች መሆናቸው ተገልጿል።
በሞተር ተሽከርካሪ፣ በሜትር ታክሲና በሿሿ የሚሰሩ ወንጀሎችን ለመግታትም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቁሟል።
በአዲስ አበባ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የሕዝብ ስጋት እንዳይሆኑና ከተማዋን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሏል።
የተሰረቁ ሞባይሎችን በሚቀበሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በመገንዘብ የመዲናዋ ነዋሪዎች ፖሊስ እየወሰደ በሚገኘው ኦፕሬሽን ሂደት ውስጥ መረጃ በመስጠትና በመጠቆም እገዛ ማድረግ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ነዋሪዎች ያላንዳች ስጋት በሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ላይ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጨምሮ የሁለቱም ተቋማት የፖሊስ ኃላፊዎች የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።