ቀጥታ፡

በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተግባራዊ በተደረጉ አዳዲስ የለውጥ እርምጃዎች መነቃቃት አሳይቷል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተግባራዊ በተደረጉ አዳዲስ የለውጥ እርምጃዎች መነቃቃት ማሳየት መቻሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።   

ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚረዳ የባለድርሻ አካላት ፎረም አካሂዷል።    

በፎረሙ ላይ የኢንቨስትመንት  ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ  ዶክተር አሰግድ  ጌታቸው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ  አባል አምባሳደር  ዲና ሙፍቲ ተሳትፈዋል። 


 

የክልል  ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሀላፎዎች እና ከተማ  መስተዳድር  ከንቲባዎችና ምክትል ከንቲባዎች፣ ባለሃብቶችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት  በፎረሙ ላይ ተሳትፈዋል።

ፎረሙ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚያመርቱ ኢንቨስተሮች የሚገጥማቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንደሆነም ተገልጿል።


 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ  አክሊሉ ታደሰ  እንደተናገሩት፤ ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮች ተግባራዊ አድርጓል።     

ለአብነትም ከዚህ ቀደም የተመረቱ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቶች ገበያ የሚያፈላልጉት ራሳቸው አምራች ኩባንያዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት አሠራሩ ተቀይሮ ኮርፖሬሽኑ ገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ በሰፊው መግባቱን አብራርተዋል።    

ከዚህ ባለፈም ኢንቨስትመንትን በማስተዋወቅና በመሳብ በኩልም ቡድን ተዋቅሮ በተለያዩ አህጉራት ማስተዋወቅ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል።

ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ኢንቨስትመንቱ እየተነቃቃ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በ2014 በጀት ዓመት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የገቡ ባለሃብቶች ከ12 ያልበለጡ ሲሆን፤ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 53 አዳዲስ ባለሃብቶች መሳብ መቻሉን ማሳያ ነው ብለዋል።    

በአሁኑ ወቅትም ካሉት 177 ሼዶች ውስጥ 157 የሚሆኑት በባለሃብቶች መያዛቸውን ጠቅሰው፤ አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ በባለሃብቶች መያዛቸውንም አክለዋል።    

ከዚህ ቀደም ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአመዛኙ ጨርቃጨርቅና ጋርመንት ላይ ያተኮሩ ምርቶችን እንደሚያመርቱ አስታወሰው፤ በአሁኑ ወቅት የምርት ስብጥሩን ወደ ግብርና ማቀነባበር፣ መኪና መገጣጠሚያና ማምረቻ እንዲሁም መድኃኒት ምርት ማስፋት ተችሏል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ አስናቀ ታምሩ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ባለሃብቶች በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ሥራቸው እንዳይስተጓጎል ጥረት እያደረገ ነው።   

አገልግሎቱ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ባለሃብቶች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።    

ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዚህ በፊት ኃይል የሚያገኙት በአየር ላይ በተዘረጋ ኬብል መሆኑን አስታውሰው፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሬት ለመሬት በሚቀበር ኬብል ኃይል እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራት ተጀምረዋል ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተመረቱ ምርቶች ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።  

 

  

 

 

 

 

 

    

 

 

 

   

 

 

 

  

 

        

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም