የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በቅርቡ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በቅርቡ ይጀምራል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በቅርቡ እንደሚጀምር ገለጸ።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትና ቀጣይ እቅዶችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አሁኑ ላይ 700 ወረዳዎች ተሳታፊዎችን የመለየትና አጀንዳ ኃሳብ የሚሰጡ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ 327 ወረዳዎች የአጀንዳ ኃሳብ የሚሰጡ ተወካዮቻቸውን ሙሉ ለሙሉ መርጠው መጨረሳቸውን ነው ያብራሩት።
የተሳታፊ ልየታና ተወካዮቻቸውን የመምረጥ ሥራው በተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በትግራይና አማራ ክልል ተሳታፊዎችን ለመለየት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን በመጠቆም።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፤ ተሳታፊዎች በማሳተፍ የአጀንዳ ሃሳቦችን ወደ መሰብሰብ ምዕራፍ በቅርቡ ይጀመራል።
የአጀንዳ ኃሳብ የሚሰበሰበው በዋናነት ከኅብረተሰቡ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃም የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በጥናት ለይተው ለኮሚሽኑ የሚያመጡበት አግባብ ይኖራል ብለዋል።
አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆንና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በገጽ ለገጽ፣ በቢል ቦርዶች፣ በሕዝባዊ ቅስቀሳና ሌሎች የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች የምክክሩ አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታት በጋራ ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት እውን እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።