ቀጥታ፡

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል ከአጋር አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል ከአጋር አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር "ፍሪደም ፈንድ" ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሰው የመነገድ ወንጀልን በጋራ ለመከላከል የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከፍሪደም ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ዳንኤል መለሰ ጋር ተፈራርመዋል።


 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሰዎች ፍልሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።

መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሚደረገው ፍልሰት የሚሄዱ ወገኖች ለበርካታ ጥቃቶች እንደሚጋለጡ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሕጎቿ አካል ማድረጓን ጠቁመዋል።

ሕገ-ወጥ ደላላዎች እና አዘዋዋሪዎች እንዲሁም የግንዛቤ እጥረት ወንጀሉን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ፈተና መሆናቸውን አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል መረጃዎችን የማደራጀት እንዲሁም ፍልሰት በሚበዛባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ትልልቅ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል።

እንዲሁም ከተለያዩ አገራት ከስደት የተመለሱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ረገድም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

እነዚህ ሥራዎች በመንግሥት ብቻ የሚተገበሩ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ ስምምነቱ በቅንጅት የሚሰሩ ሥራዎችን ለማገዝ መሆኑን አመላክተዋል።

"ፍሪደም ፈንድ" በሰዎች መነገድ ወንጀል፣ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ስራን ለመከላከል የፋይናንስ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ስምምነቱም የትብብር እና የቅንጅት አሠራርን በማጎልበት የጉልበት ብዝበዛና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የፍሪደም ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ዳንኤል መለሰ በበኩላቸው፤ ፍሪደም ፈንድ በፍልሰት ጉዳዮች ላይ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተከታታይ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።

ስምምነቱ ለሦስት ዓመታት የሚተገበር እና በየዓመቱ በሚገኙ በጀት እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ማሳለጥ እንዲሁም ከእድሜያቸው ውጭ የጉልበት ብዝበዛ የሚደረግባቸውን መታደግ የስምምነቱ ዓላማዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ 56 ሺህ ዜጎችን ቀጥታ ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ አለው ብለዋል።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል  የብዙ ተቋማትን የቅንጅት ስራ የሚጠይቅ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ  የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው። 


 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት ቢደረግም በትብብር የምንሰራበት ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም