የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ልማት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የአገርና የህዝብ አለኝታ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ልማት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የአገርና የህዝብ አለኝታ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ልማት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የአገርና የህዝብ አለኝታ መሆኑን የሚያረጋግጡ መሆናቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተለያዩ ውጣ-ውረዶችን በድል እየተሻገረ የአገሪቱን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅና ሉዓላዊነቷን በማስከበር 88 ዓመታት አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈም በተለያዩ አገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጁን በብቃት በመወጣት ትልቅ ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
በመንግሥታት መቀያየር ምክንያት አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ እያለ 88 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ ዛሬ ላይ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ የኢትዮጵያ አስተማማኝ የአየር ክልል ዘብ መሆኑን አስመስክሯል።
አየር ኃይሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን በሰው ኃይል፣ በመሠረተ- ልማትና በቴክኖሎጂ ጠንካራ አቅም መፍጠር ችሏል።
ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ የውጊያ አውሮፕላኖችን ጠግኖ ጥቅም ላይ ማዋልን ጨምሮ በሰው ኃይልና በውጊያ መሠረተ-ልማት ግንባታ የተሰሩ ሥራዎች በሪፎርሙ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸው በአየር ኃይሉ ከፍተኛ አዛዦች ተገልጿል።
በቅርቡ የአየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ሲከበር የተከናወኑ ኹነቶችም ተቋሙ የፈጠረው አቅም የላቀ መሆኑን አመላክተዋል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኤሮስፔስ መምህርና የምህንድስና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ድንቁ ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው።
አየር ኃይሉ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥም በትክክለኛ ተቋማዊ ግንባታ ላይ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ተቋሙ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ልማት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የአገርና የህዝብ አለኝታ መሆኑን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም እየመራ ባለው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ረገድ ከዚህም በላይ የተጠናከረ የምህንድስና ሥራ ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።
ለዚህም መንግሥት አየር ኃይሉን በተሟላ መንገድ ለማዘመን የሚያደርገው እገዛ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ ዓለም የደረሰበትን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በማጠናከር ተቋማዊ አቅሙን በላቀ ደረጃ ማጎልበት ይገባዋል ብለዋል።
የዓለም ኃያላን ሀገራት የመከላከያ ተቋሞቻቸው የእድገታቸው መሠረቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ለውጥ ለማምጣት መንግሥት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና መሰል ተቋማት ዘርፉን ማገዝ እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ለዚህም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ-ትምህርት በመቅረፅ ከመከላከያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ዘርፉን የሚያግዝ የሰው ኃይል ለማሟላት በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል ብለዋል።