ደም መለገስ የሰዎችን የነገ ሕይወት የሚያስቀጥል ዋጋ የማይተመንለት ውድ ስጦታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ደም መለገስ የሰዎችን የነገ ሕይወት የሚያስቀጥል ዋጋ የማይተመንለት ውድ ስጦታ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 12/2016(ኢዜአ)፦ደም መለገስ የሰዎችን የነገ ሕይወት የሚያስቀጥል ዋጋ የማይተመንለት ውድ ስጦታ መሆኑን ደማቸውን ለበርካታ ጊዜ የለገሱ በጎ ፈቃደኞች ገለጹ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 118 ነጥብ 5 ሚሊየን የደም ልገሳዎች እንደሚካሄዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህ ውስጥ 40 በመቶው ደም የሚሰበሰበው ከፍተኛ ገቢ ባላቸውና ከዓለም 16 በመቶ ሕዝብ ባለባቸው አገራት ነው።
አማካይ የደም ልገሳ ምጣኔ ሲታይም ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ልገሳ ምጣኔ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው በዘጠኝ እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑ ይጠቀሳል።
በብዙ አገራት ያለው የደም ፍላጎት ከአቅርቦት የተመጣጠነ አለመሆኑ እንደ ትልቅ ፈተና የሚታይ ሲሆን፤ በቂ የደም አቅርቦትን ማረጋገጥ የሚቻለው በዘላቂነት በሚደረግ የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርኃ-ግብር እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ይሰማል።
አቶ ዳዊት ተስፋዬ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ደም መለገስ የጀመሩት በ1983 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት ወቅት እንደሆነ ያስታውሳሉ።
በሕክምና ተቋማት ሕክምና ለማግኘት የሚመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደም ለማግኘት ሲቸገሩ ማየታቸው በመደበኛነት ደም ለመለገስ ምክንያት እንደሆናቸው ገልፀዋል።
በ32 ዓመታት ውስጥ 96 ጊዜ ደም መለገሳቸውን ጠቁመው፤ የሰውን ልጅ ከሞት ለመታደግ በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጽዖ በማበርከታቸው የሕሊና ሰላም እንደሚሰማቸው አመልክተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ደም የመለገስ ልምድ እየዳበረ ቢመጣም ቀጣይነት ባለው መልኩ የጀመሩትን በጎ ሥራ ዘላቂነት ባለው መልኩ የመቀጠል ክፍተቶች እንዳሉ ነው አቶ ዳዊት የገለጹት።
ማንኛውም ሰው በደም እጦት ምክንያት እንዳይጎዳ ደም መለገስን መደበኛ ተግባሩ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ደም መለገስ የሰው ልጅ በቀናነት የሚያከናውነው ሰብዓዊ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ለ95 ጊዜ ደም የለገሱት ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ ናቸው።
ነዋሪነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት ሲስተር አሰጋሽ፤ ደም መለገስ ማንኛውም ጤነኛ የሆነ ሰው ሊያከናውነው የሚገባ ተግባር ነው ይላሉ።
ደም መለገስ የአዕምሮን ሰላም የሚሰጥና ጤናን የመጠበቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ዜጎች ደም በመለገስ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሕይወት በመድረስ በመልካም ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሃብታሙ ታዬ፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አሁን ላይ ስለ ደም ልገሳ ያለው አመለካከት ለውጥ እየታየበት መሆኑን ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት እንደ አገር እየጨመሩ ከመጡት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጋር ተያይዞ የጤና ተቋማት የደም አቅርቦትን የማግኘት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።
የደም አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበውን ደም መጠን ለመጨመር ከተለያዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ከ140 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ማግኘቱን ነው አቶ ሃብታሙ የጠቆሙት።
ዜጎች ደም በመደበኛነት የመለገስ ባህላቸውን በማሳደግ ለሌሎች ሕይወት እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት በ2016 በጀት ዓመት ከ427 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ለመሰብሰብ ማቀዱን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አንድ ጤናማ የሆነ ሰው በዓመት ውስጥ በመደበኛነት ሦስት ወይም አራት ጊዜ መስጠት እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ የሚያሳይ ሲሆን፤ ድርጅቱ ማንም ሰው በደም እጦት መሞት የለበትም የሚል መርህ አለው።