ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለድኅረ-ምርት አሰባሰብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር የአየር ሁኔታ ይኖራል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለድኅረ-ምርት አሰባሰብ አመቺ የሚሆን የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የመኸር ሰብል አምራች ለሆኑ አካባቢዎች ለድኅረ-ሰብል አሰባሰብ አመቺ ነው።

አርሶ አደሩ አመቺ የሆነውን የአየር ሁኔታ በመጠቀም ሰብሉን በፍጥነት እንዲሰበስብ ትንበያው አመልክቷል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚቀጥልና በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ የደመና ክምችት እንደሚኖር ትንበያው አመልክቷል።

በተለይም በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ የሲዳማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል።

የተገኘው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑትና ጥምር ግብርና ለሚያካሂዱ የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በተጨማሪም በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን እንደሚኖረውም መረጃው ያሳያል።

በእነዚህ ቀናት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያው አመልክቷል።

በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በመካከለኛውና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ሊኖር እንደሚችል ትንበያው ጠቁሟል።

ይህ ሁኔታ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተብሏል።

በሌላ በኩል በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የገፀ-ምድር ውሃ መጠን እንዲሻሻል የሚያግዝ እንደሆነም ትንበያው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም