ቀጥታ፡

ሙስናና ሌብነትን ለማስወገድ የፍትህ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል

አዳማ፤ ታህሳስ 12 / 2016(ኢዜአ)፡- የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑት  ሙስናና ሌብነትን ለማስወገድ የፍትህ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው  የፍትህ ሚኒስቴር አስገነዘበ።

የፌዴራልና የክልሎች የፍትህ አካላት በአገር አቀፍ የፍትህና የዳኝነት ሪፎርም ላይ የሚመክር የጋራ መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ህዝቡ በፍትህ ስርዓትና በዘርፉ ተቋማት ላይ ጠንካራ አመኔታ እንዲኖረው ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር አለበት።

በተለይም የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑት እንደ ሙስና፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር እንዲሁም የዜጎች የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ የፍትህ አካላት ሚና የማይተካ መሆኑን ተናግረዋል።

በፍትህ ዘርፉ ያሉ ሙያተኞችን በስነምግባር፣ በዕውቀትና ክህሎት ብቁ ከማድረግ አንፃር እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች አመርቂ ውጤት እየተገኘባቸው አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም ከዘርፉ ተግዳሮቶች መካከል ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ወጪ ቆጣቢ የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመምራት አንፃርም ድክመቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

የፍትህ ዘርፉ   አሁንም ከዘልማድ አሰራር ያልተላቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም የኢትዮጵያ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና ፎኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።


 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ የፍትህ አገልግሎቱን ለማሳለጥና የህብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በዳኝነት፣ በፍትህ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዘርፉ  ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም ከፌዴራል የፀጥታና ፍትህ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ቅንጅታዊ አሰራር የሚመራበትን ቻርተር በማፅደቅ እየሰሩ መሆናቸውን አክለዋል።

በተመሳሳይ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንሲ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር የተለያዩ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን በሚያዘምኑ ስራዎች ላይ በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በተሰናዳው በዚሁ መድረክ ላይ ከፌዴራልና ከክልሎች  የተውጣጡ የፍትህ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም