ቀጥታ፡

የባህር በርና የአማራጭ ወደብ ጥያቄ ተገቢነት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጥ አቋም መያዝ እንደሚገባው ተገለጸ

አርባ ምንጭ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የባህር በርና የአማራጭ ወደብ ጥያቄ ተገቢነት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጥ አቋም በመያዝ የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ መስራት እንዳለበት ተገለጸ።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ "የባህር በር የልማት በር" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደብ ዙሪያ የምሁራን ውይይት እየተደረገ ነው።

በፕሮግራሙ ላይ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደብ ጥያቄ ተገቢነት ላይ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብና ምሁራን አንድ መሆን አለባቸው።


 

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባህር በርና ወደብ ተጠቃሚ እንደነበረች ጠቅሰው የአካባቢው የጂኦፖለቲካ አለመረጋጋት ይህንን ጥቅሟን እንዳሳጣት ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የማንሳት ታሪካዊ፣ መልክአ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መብት እንዳላት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እያነሳች ያለችው የባህር በርና አማራጭ ወደቦች ጥያቄ ለማሳካት ከምንም በላይ የሰላም አማራጮችን መጠቀም እንዳለባት ጠቅሰው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከ12 ወንዞች በላይ ለአካባቢው ሀገራት እያበረከተች የባህር በር ተጠቃሚ አለመሆኗ ተገቢ አይደለም ያሉት ዶክተር ዳምጠው ምሁራንና ህዝቡ በየደረጃው በዚህ አጀንዳ ላይ መወያየት እንዳለበትም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እያላት የባህር በር ተጠቃሚ አለመሆኗ ኢፍትሃዊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ዘርፍ ምሁር ዶክተር አብደላ ከማል ናቸው።

"በዚህም ምክንያት ከውጭ ለምታስገባው ምርት ለባህር በር ከፍተኛ ኪራይ እየከፈለች በመሆኑ በዕድገቷ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ30 ዓመት በኋላ እጥፍ እንደሚያድግ የጠቀሱት ምሁሩ የባህር በርና አማራጭ ወደብ ጥያቄ ከወዲሁ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለተገቢነቱ ደግሞ ከበቂ በላይ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰዉ ምሁራን በዚህ ጉዳይ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ለአንድ ቀን በሚቆየው ፓናል ላይም በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነት፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ህግና ጂኦፕለቲካዊና የውጭ ግንኙነት አንጻር እንዲሁም በቀይ ባህር አካባቢ ባሉ አዳዲስ ፍላጎቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

 

 

 

 

 
 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም