ቀጥታ፡

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በቀይ ባህርና የኢትዮጵያ ፍላጎት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አዘጋጀ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ) ፡- "ቀይ ባህር እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ መሻት አንድምታዎች" በሚል ርዕሰ ጉዳይ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ነገ በሰመራ ይካሄዳል።

አውደ ጥናቱን የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑን በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖሊቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና የአውደ ጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ጀማል ሙሀመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።

አውደ ጥናቱ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አስፈጻሚ አካላት እንዲሁም ተማሪዎች ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላትን ሁለገብ ብሔራዊ ጥቅም፣ መልካም አጋጣሚዎች እና ተግዳሮቶች እንዲመረምሩ እና እንዲወያዩበት መድረክ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል። 

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች እውቀታቸውንና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ፣ አዳዲስ ሀሳቦችን እንዲያነሱ በማድረግ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ህትመት ስነምግባርና ስርፀት ዳይሬክተር ዶክተር ኡመር አብዱልቃድር፤ በአውደ ጥናቱ  የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከታሪክ፣ ከዓለም አቀፍ ህግ፣ ከጂኦፖለቲካ እንዲሁም ከቀጣናዊ ውህደትና የንግድ ትስስር አንጻር ያለውን ተገቢነትና ያሉ ዕድሎችን የሚዳስሱ ሀሳቦች በምሁራን ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስለባሕር በር አስፈላጊነት በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድርና በኢኮኖሚ ላይ በመመስረት የባህር በር የማግኘት ሕጋዊ መብት እንዳላት አስረድተዋል።

ለስኬቱም የባህርተኝነት ራዕይ መፍጠርና ማዳበር፣ ድንበር ተሻጋሪ የማህበራዊ ትስስርን ማጎልበትና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አጽንኦት የሰጡት ጉዳይ ነው።

በአውደጥናቱ ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ ተመራማሪዎች፣ የመንግስት አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም