ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቅርቡ አጀንዳ ወደ መስብሰብ ስራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቅርቡ አጀንዳ ወደ መስብሰብ ስራ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቅርቡ አጀንዳ ወደ መሰብሰብ ምዕራፍ እንደሚገባ አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ እያከናወነ ባለው ተግባርና ቀጣይ በሚሰራቸው ስራዎች መግለጫ ተሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የተሳታፊ ልየታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንና በቅርቡ አጀንዳ ወደ መሰብስብ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በንቃት በመሳተፍ ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ በመገናኛ ብዙሀን፣ በገጽ ለገጽ፣ በህዝባዊ ቅስቀሳ፣ በህትመትና ሌሎች የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ በመጀመር በመላው አገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የተሳታፊ ልየታን በተመለከተ በሁለት ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን በመግለፅ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁና በሂደት ላይ ያሉትን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከትግራይ እና አማራ ክልል ውጭ በአገሪቱ 700 ወረዳዎች ላይ ተሳታፊዎች የመለየት ወይንም ደግሞ ወኪሎቻቸውን የመምረጥ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ተሳታፊዎችንና የአጀንዳ ሀሳብ የሚሰጡ ተወካዮችን ለማስወከል ባደረገው ጥረት በ327 ወረዳዎች ላይ ሀሳብ የሚሰጡ ተወካዮቻቸውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቀዋል።
የዲያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተ በመካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካና በሌሎች የአለም አገራት ላይ ከሚገኙ ዲያስፖራዎች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይ በአውስትራሊያና ሌሎች የአለም አገራት ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።