ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በሚካሄደው 20ኛው የአፍሪካ የቡና ጉባኤ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በመጪው የካቲት ወር በሚካሄደው 20ኛው የአፍሪካ የቡና ጉባኤ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ጉባኤው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከአፍሪካ ፋይን ኮፊ ማኅበር ጋር በመሆን እንደሚያዘጋጁትም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፤ ለቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባኤ አውደ ርዕይ፣ የቡና ቅምሻዎችና የፓናል ውይይቶችና ሌሎች ተያያዥ መርኃ ግብሮች ይኖራሉ ብለዋል።

በዚህ ጉባኤ ከ2 ሺህ በላይ የቡና ነጋዴዎች፣ ላኪዎችና አምራቾች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በጉባኤው የኢትዮጵያን ቡና ማስተዋወቅና ከምርቱ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በጉባኤው ቡና አምራቾች ምርታቸውን ለማስተዋወቅና ለማሻሻጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የቡና አምራቾችንና ላኪዎች ከዓለም የቡና ገበያ ጋር ትስስር ለመፍጠር ያስችላልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ብራንዱን በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናነወነ መሆኑን ጠቁመው አገሪቱ በዘርፉ የምትሰራቸውን ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

በጉባኤው ለመሳተፍ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ የዘርፉ ተዋናያንን ለማስተናገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በጎባኤው ለመሳተፍ ለሚመጡ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ20 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ቤልጂየም፣ ጀርመንና ሳኡዲ አረቢያ የኢትዮጵያ የቡና መዳረሻ አገራት ሲሆኑ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ አገራት ወደ 60 አድጓል ተብሏል።

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት 1 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ እየሰራች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም