በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልዑካን ቡድን ከቻይናዋ ሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ከሆኑት ዙ ሹንዚው ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልዑካን ቡድን ከቻይናዋ ሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ከሆኑት ዙ ሹንዚው ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፤ ታህሣሥ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልዑካን ቡድን ከቻይናዋ ሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ከሆኑት ዙ ሹንዚው ጋር ተወያይቷል።
የሱቿን ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ቼንዱ ከተማ ለፓርክ እና ከተማን አረንጓዴ ለማድረግ የተገበሩት እጅግ የተዋጣለት የ"ፓርክ ከተማ" ጽንሰ-ሀሳብ እና የአረንጓዴ ከተማ ስርዓት ግንባታ የሚደነቅ እና ለሌሎች ምሳሌ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል።
ከብዙ የአለም ሀገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ግንኙነት ካላት የቼንዱ ከተማ የከተማ ልማትን ከፓርክ ጋር በማስማማት ለከተሞች አዳዲስ ገጽታ በመፍጠር ረገድ እና አሮጌውን በማደስ ያላቸው መልካም ልምድ ማግኘታቸውን ከንቲባ አዳነች ጨምረው ገልፀዋል።
ትልቋ የቡና አምራችና ላኪ ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ሌጋሲ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በመስራት ላይ እንደምትገኝም ከንቲባዋ አብራርተዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች ያሉት ከንቲባ አዳነች የቻይና ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣይ ኢትዮጵያን ለቻይና ጎብኚዎች ከተመረጡት መዳረሻዎች አንዷ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ዙ ሹንዚው በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት ወደ በማንኛውም ሁኔታ ፀንቶ የሚቆይ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት (All-weather Strategic Cooperation Partnership) ማደጉን አስታውሰዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ጋርም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በገቢና ወጪ ንግድ፣ በቱሪዝም፣ በቴክኒክ ሙያ ትምህርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በትብብር ለመስራት የእህትማማችነት ስምምነት ለመፈራረም እንደሚፈልጉ ምክትል ሰብሳቢዋ መግለጻቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ግንኙነታችን ይበልጥ እንዲጠናከር የሱቿን ግዛት ከአዲስ አበባ ጋር የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብለው በተጨማሪም የሀዋሳ ከተማ ከቼንዱ ከተማ ጋር የእህትትማማች ግንኙነት እንድትመሰርት ጥያቄ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ግንኙነታችንን ይበልጥ እንዲጠናከር አዲስ አበባ ከሱቿን ግዛት ጋር እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከቼንዱ ከተማ ጋር የእህትትማማች ግንኙነት በመመስረት በንግድ፣ በኢኮኖሚ፣ በከተማ ልማት፣ በህዝብ ለህዝብ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት ሁለቱም አካላት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።