"የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" የሕዝብን ትስስር የሚያጠናክር በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
"የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" የሕዝብን ትስስር የሚያጠናክር በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ)፦ "የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" የሕዝብን ትስስር የሚያጠናክር በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለዓለም ለማስተዋወቅ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌና የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳዳሪዎች ገለጹ።
የጉራጌ ህዝብ ባህላዊ የዳኝነትና አስተዳደር ስርዓት የሆነውን "የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" በዓለም ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።
በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት የቆየውን ባህላዊ የዳኝነትና አስተዳደር ስርዓት የሚመራው "የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" ዓመታዊ ጉባዔ የጉራጌና የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በታደሙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ጥቅም ላይ ሲውል እንደነበር የሚነገርለት የጉራጌ ባሕላዊ ሸንጎ በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭት ለማርገብ፣ ቂም በቀልን ለማሻር፣ ሕይወትና ንብረት ለመጠበቅ ብሎም ጤናማ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠርና ፍትሕን ለማስፈን የሚያገለግል የዳኝነት ስርዓት ነው።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ፤ የጉራጌ ባህል ሸንጎ የጉራጌ ሕዝብን የሚያስተሳስር ትልቅ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።
የሽምግልና ሥርዓቱ የጉራጌን የከበረ ባህል ያሳየና ለዘመናት የቆየ የሕዝብ አንድነት እንዲጠበቅ ያደረገ እሴት መሆኑን ገልፀዋል።
ለበርካታ ምዕተ ዓመታት የዘለቀው የጉራጌ ባሕላዊ ሸንጎ መላው ማህበረሰቡ የሚዳኝበት የግጭት አፈታትና አስተዳደር ስርዓት መሆኑን ገልጸው በታሪክ በጉልህ ሊጠቀስ የሚገባው ቅርስ ነው ብለዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው፤ አባቶች እና ጉባዔተኞች የጉራጌ ሕዝብ አንድነትና አብሮነት እንዲጎለብት በጋራ እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
የጉራጌ ማህበረሰብ በየደረጃው ያሉ ግጭቶችና የፍትህ መጓደሎችን ለማረቅ ዛሬም ለሚነሱ ግጭቶች ቁልፍ መፍትሔ አድርጎ እያገለገለበት መሆኑን ገልጸዋል።
የጉራጌ ባህልና እሴቶች፣ ታሪክና ቅርሶችን ማዳበርና ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት በመሥራት የቱሪስት መስህብ እንዲሆንና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዲያድግ መረባረብ እንደሚገባ ነው የጠቀሱት።
የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ ባለው ጠንካራ ባህላዊና ትውፊታዊ መሠረት በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የታፈረ ሥርዓት እንደሆነ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መመሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት አመርጋ ለኢዜአ ገልፀዋል።
እንደየአካባቢው "የኧጆካ ቕጫ"፣ "የጎርደና ሴራ"፣ "የፈር አገዘኘ ሴራ" እንዲሁም "የዶቢ ጎጎት ስናኖ ሴራ" በመባል የሚጠራው የጉራጌ ሸንጎ ከአራት ዓመታት በፊት ሁሉንም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶች የሚወክል 'የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" እንደ ተቋም በይፋ መቋቋሙን አስታውሰዋል።
የራሱ መተዳደሪያ ደንብ ያለው የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ 60 ጠቅላላ ጉባዔ አባላት እና ለሦስት ዓመታት በምርጫ የሚያገለግሉ የ15 ሥራ አስፈጻሚ አባላት እንዳሉት ጠቁመዋል።
ይህን ድንቅ እሴት ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማውረስ እንደ ተቋም ትልቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የጉራጌ ባሕላዊ ሸንጎን ከብሔራዊ ደረጃ ባሻገር በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ እና ከጉራጌ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር በተሰሩ ስራዎች የጥናትና የሰነድ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።
ባለስልጣን ከመላው ኢትዮጵያ በሚቀርቡለት የቅርስ ምዝገባ ጥያቄዎች መሰረት ተራቸውን ጠብቆ ለዩኔስኮ እስከሚያቀርበው እየተጠባበቁ መሆኑንም ነው የተናገሩት።