ዳያስፖራው በሀገር ቤት የተፈጠሩ ዕድሎችን መጠቀምና ተሳትፎውን ማጠናከር ይገባዋል - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በሀገር ቤት የተፈጠሩ ዕድሎችን መጠቀምና ተሳትፎውን ማጠናከር ይገባዋል - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ዳያስፖራው በሀገር ቤት የተፈጠሩ ዕድሎችን መጠቀምና ተሳትፎውን ማጠናከር ይገባዋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ዳያስፖራው በሀገር ቤት የተፈጠሩ ዕድሎችን መጠቀምና ተሳትፎውን ማጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
ይህ የተገለጸው በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ዳያስፖራ ማህበራት አመራሮች፣ በተለያየ መስክ ከተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲሁም በልማትና በኢንቨስትመንት ተሳታፊ ከሆኑ የዳያስፖራ አባላት ጋር በተዘጋጀ የዳያስፖራ የውይይት መድረክ ነው።
በመድረኩ በአገራችን የሚከሰቱ የውስጥ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት መንግስት እያከናወናቸው ስላሉ ስራዎች በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት አብራርተዋል።
እንዲሁም የሀገራችን የባህር በርና ወደብ አጠቃቀም መብትን በተመለከተ ከዳያስፖራ አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎችም አምባሳደር ምስጋኑ ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸውን በጄኔቫ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቋሚ ሚሲዮን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የዳያስፖራ አባላቱም ወቅታዊ መረጃን ከሚመለከተው አካል በቀጥታ ለማግኘት የቻሉበት መድረክ በመመቻቸቱ መደሰታቸውን በመግለጽ እንደቀደመው ሁሉ አገራቸውን በሚችሉት ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጄኔቫ የኢፌዴሪ መንግስት ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው
በቀጣይም ከሚሲዮኑ ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ስራዎችን በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዳያስፖራ አባላቱ በውይይቱ ለነበራቸው የነቃ ተሳትፎ አመስግነው ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤቱም ለዳያስፖራው ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመድረኩ አረጋግጠዋል፡፡