ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከብሪክስ የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት የፋይናንስ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ላይ አበክራ መስራት አለባት - የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ ከብሪክስ የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት ከአባል አገራት ጋር በሚጣጣም መልኩ የፋይናንስ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ላይ አበክራ መስራት እንዳለባት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን "ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ምን ትጠቀማለች?" በሚል ያጠናውን ጥናት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።


 

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የምርምርና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ዶክተር ደግዬ ጎሹ እንዳሉት፤ ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት በብዙ መመዘኛዎች የታለመለትን ዓላማ እያሳካ አይደለም።

ለአብነት የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የአስተዳደር ዘርፍ 37 በመቶ የሚሆነው የተያዘው በአምስት ሀገራት ሲሆን የ162 ሀገራት ድርሻ ከ30 በመቶ በታች መሆኑን አንስተዋል።

በንግድ፣ በወጭ ገቢ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በሌሎችን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መለኪያዎች ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት ፍትሀዊ አይደለም ብለዋል። 

በዚህም ሀገራት እኩል ድምጽ እንዲኖራቸውና በሰው ሀብት ልማት፣ በኢንፎርሜኝን ኮሙኒኬሽን፣ በልማት ፋይናንስና መሰል ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ በማለም ብሪክስ መመስረቱን  አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ጋር በብድርና በመሰረተ ልማት ግንባታ የተሳሰረች መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ ብሪክስን መቀላቀሏ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ብሪክስ በብዙ መመዘኛዎች ጠንካራና የተሻለ ጥምረት መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላት ሰፊ እድል መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከብሪክስ የሚገባትን ጥቅም ለማረጋገጥ በተለይ ተቋማት ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን ስትቀላቀል ትልቅ ዓላማ ይዛ ነው ያሉት ዶክተር ደግዬ፤ በሰው ኃይል ልማት፣ በኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባታል ብለዋል።

ለዚህም የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ የፋይናንስ ስርአቱን ማዘመንና ተወዳዳሪ ማድረግ ላይ ያተኮሩ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከብሪክስ አባል አገራት ጋር በሚጣጣም መልኩ የፋይናንስ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ላይ አበክራ መስራት እንደሚገባትም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በነሀሴ ወር 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ ጉባኤ የጥምረቱ አባል ሆና መመረጧ ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም